ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነገ በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት አግኝተዋል

ህዳር 27/2012 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነገ በቻይናና በጃፓን በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች የማሸነፍ ቅድሚያ ግምቱን አግኝተዋል። በቻይና ጉዋንዡ ማራቶን አትሌት ሙሉ ሰቦቃ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን እንዳገኘች የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስፍሯል። አትሌት ሙሉ ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም በቻይና ኩንሚንግ ዓለም አቀፍ ማራቶን አሸናፊ የነበረች ሲሆን በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ትሮጣለች። የ35 ዓመቷ አትሌት የነገ የማራቶን ውድድሯ እ.አ.አ በ2019 አምስተኛዋ ሲሆን ከኩንሚንግ ዓለም አቀፍ የማራቶን ድሏ በተጨማሪ በቻይና የዳሊያን ዓለም አቀፍ ማራቶንም አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የዴጉ ማራቶን ሁለተኛ፤ በቻይና ቤጂንግ ማራቶን ደግሞ ሶስተኛ ወጥታለች። አትሌት ሙሉ ሰቦቃ እ.አ.አ በ2015 በዱባይ ማራቶን 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷን አስመዝግባለች። አትሌቷ እ.አ.አ በ2016 ጉዋንዡ ማራቶን አራተኛ የወጣች ሲሆን ነገ በደቡብ ቻይና ከተማ በሚካሄደው ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ወስዳለች። ኬንያዊቷ አትሌት ሴሊስቲን ቼፕቺርቺር የአትሌት ሙሉ ሰቦቃ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚትሆን የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል። አትሌት ህይወት ገብረኪዳን በውድድሩ ላይ የምትሳተፍ ሲሆን እ.አ.አ በ2017 በእስራኤል ሲ ጌ ናዝሬት 2 ሰአት ከ25 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰአቷን አስመዝግባለች። በወንዶቹ ውድድር አትሌት ገብረጻዲቅ አብርሃ የሚሳተፍ ሲሆን ኬንያውያን አትሌቶች ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል። አትሌት ገብረጻዲቅ እ.አ.አ በአምስተርዳም ማራቶን 2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱን አስመዝግቧል። በውድድሩ በወንዶች ከ2 ሰአት ከ9 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ በታች በሴቶች ከ2 ሰአት ከ26 ደቂቃ በታች በመግባት ካሸነፉ የ40 ሺህ ዶላር ተጨማሪ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል። በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ስምንት ለሚወጡ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል። ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደው የጉዋንዡ ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ያገኘ ውድድር ነው። ባለፈው ዓመት የጉዋንዡ ማራቶን በሴቶች አትሌት ትዕግስት ግርማ፤ በወንዶች ሞሮኳዊው አትሌት ሞሐመድ ዚያኒ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል ነገ የሴት አትሌቶች ውድድር ብቻ የሆነው የጃፓን ሳይታማ ዓለም አቀፍ ማራቶን አትሌት በላይነሽ ኦልጅራ የማሸነፉን የቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች። አትሌት በላይነሽ እ.አ.አ በ2018 በጀርመን ፍራንክፈርት ማራቶን 2 ሰአት ከ21 ደቂቃ ከ53 ሴከንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው። ረሂማ ቱሳ፣ ፋጡማ ሳዶ፣ ዝናሽ ደበበና ዘርፌ ልመንህ በነገው ወድድር ላይ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። የጃፓንና ኬንያ አትሌቶች የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋነኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል። ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሳይታማ ዓለም አቀፍ ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የብር ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው። ባህሬናዊቷ አትሌት ዳሊላ አብዱልቃድር የባለፈው ዓመት የሳይታማ ዓለም አቀፍ ማራቶን አሸናፊ እንደነበረች የሚታወስ ነው። የሳይታማ ዓለም አቀፍ ማራቶን እ.አ.አ በ2015 ሲጀመር አትሌት አጸደ ባይሳ የመጀመሪያዋ አሸናፊ ነበረች።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም