የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ገቡ

88
ህዳር 27/2012  አዲሷ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማደረግ ዛሬ ጧት አዲስ አበባ ገብተዋል። ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ለየን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ኡርስላ ቮን ደር ለየን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኮሚሽን መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል። ኡርሱላ ቮን ደር ለየን በቅርቡ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ወዲህ ከአውሮፓ ሀገራት ውጭ የመጀመሪያ የሆነውን ጉብኝታቸውን ነው በኢትዮጵያ የሚያደርጉት። የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ይፋዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1967 ዓም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ እንዲሁም ከካሪቢያንና ከፓስፈክ አገሮች ጋር በሎሜ በደረሱት የኮቶኖ ስምምነት መሰረት ነው። የአውሮፓ ህብረት በዚያው ዓመት ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ በመክፈት ግንኙነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ጠቅሷል። ኢትዮጵያም ቤልጄም ብራሰልስ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል የሁለቱን ግንኙነት አጠናክራ በማስቀጠል ላይ ትገኛለች ነው ያለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም