ቀጥታ፡

በክልሎቹና ከተማ አስተዳደሩ የልጀነት ልምሻ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መሰጠት ተጀመረ

ኢዜአ-ህዳር 26 ቀን 2012 በአፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እና በድሬዳዋ አስተዳደር ለአራት ቀን የሚቆይ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዛሬ በዘመቻ መሰጠት ተጀመረ። በዚህም እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባቱ እንደሚሰጥ ተገልጿል። የአፋር ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና የህጻናት ክትባት ባለሙያ አቶ አወል ጉደሌ ለኢዜአ እንደገለፁት ክትባቱ በሁሉም ወረዳዎች ቤት ለቤት ነው መሰጠት የተጀመረው። "ክትባቱ ከአምስት አመት በታች ለሆኑ 264 ሺህ ለሚሆኑ ህጻናት ይሰጣል" ብለዋል። የክትባቱ ስራ የተጀመረውም የሰው ኃይል፣ መድኃኒትና ሌሎችንም መገልገያዎች በማመቻቸት ነው። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም እስከ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም በሚቆየው ዘመቻ 197 ሺህ 166 ህጻናት እንደሚከተቡ ይጠበቃል። የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዋጮ ዋቡልቾ እንዳሉት ክትባቱ ከሚሰጣቸው እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ከሆኑ ህጻናት ውስጥ 12 ሺህ 542ቱ በአራት የስደተኞች ካምፖች የሚገኙ ናቸው። በክትባት ዘመቻው 1 ሺህ 100 የጤና ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች ተሰማርተዋል ። "ዛሬ በተጀመረው ዘመቻ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 61 ሺህ ህጻናት ይከተባሉ" ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ ናቸው፡፡ ኃላፊው በኢትዮ-አሊያንስ ፍራንሴስ ትምህርት ቤት ተገኝተው መርሀ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት ወላጆች ልጆቻቸውን በማስከተብ ህጻናትን ከአካል ጉዳትና ከሞት የማዳን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም