ቀጥታ፡

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የሚካሄዱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ሳምንት ተሸጋግረዋል

ኢዜአ ህዳር 26/2012 በአዲስ አበባ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሊካሄዱ የነበሩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ምክንያት ወደ ቀጣዩ ሳምንት መሸጋገራቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

በክልል ከተሞች የሚካሄዱ ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄዱም ገልጿል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰበታ ከተማ፤ ከነገ በስቲያ ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው።

ሆኖም ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚከበረው 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ምክንያት ጨዋታዎቹ ወደ ቀጣዩ ሳምንት መሸጋገራቸውን የፌዴሬሽኑ የውድድር ባለሙያ አቶ ጋሻው ረታ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ማክሰኞ ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም፤ ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባ ጅፋር ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በተመሳሳይ ከቀኑ በ11፡00 ሠዓት ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞች የሚካሄዱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግን በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ነገ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ፣ በትግራይ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከወላይታ ድቻ፣ በሆሳዕና ስታዲየም ሀዲያ ሆሳዕና ከሐዋሳ ከተማ ይጋጠማሉ።

በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየምም ፋሲል ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከስሑል ሽረ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ይጫወታሉ።

የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ ወላይታ ድቻ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ስሑል ሽረና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ድል ቀንቷቸዋል።

ሶስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች 13 ግቦች ከመረብ አርፈዋል።

በሌላ በኩል የ2012 ዓ.ም የሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይጀመራል ተብሎ ነበረ።

ነገር ግን በ14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ምክንያት የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብሮች ለአንድ ሳምንት መራዘማቸውን ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም