በኢንደስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ነው ተባለ

17
ሚዛን ሰኔ 15/2010 በኢንደስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የደቡብ ንግድና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ለደቡብ ምዕራብ ካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ ዞኖች ለተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ሰሞኑን በሚዛን አማን ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በደቡብ ክልል ንግድና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ የኢንደስትሪ ቁጥጥርና አካባቢ እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ብሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የብድር አቅርቦትና አመላለስ የውሀና የመብራት አገልግሎት እጥረት የኢንደስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ልማት ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ እንዲሁም በዘርፉ በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ሌላው ተግዳሮት በመሆኑ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተናቦ መስራት እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡ ኢንደስትሪና ማንፋክቸሪንግ ሥራ የተለያዩ አካላትን የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ የመስተዳድር አካላትና የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ካፒታል የፕላንና ፕሮሞሽን ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኦሎንጆ ኦልቆሞ በበኩላቸው በከተሞች በቂ የመብራት ኃይል አቅርቦት ችግር የውሀና ሌሎች መሰረተ ልማት ክፍተቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት 105 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 1ሺህ 165 ማሽነሪዎች ለ327 ኢንተርፕራይዞች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ''ማሽነሪዎቹ በኃይል አቅርቦትና መሰረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር አልገቡም'' ብለዋል፡፡ ማሽነሪዎቹ ለእንጨትና ብረታ ብረት፣ ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና ለልብስ ስፌት አገልግሎት  የሚውሉ ናቸው፡፡ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረገው ሽግግር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የቤንች ማጂ ዞን ንግድና ኢንደስትሪ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ስንቁ ነጋሽ በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ሁለት የማንፋክቸሪንግ ማዕከላት በጥቃቅን ችግሮች ሥራ ሳይጀምሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ማዕከላቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር እንዲገቡ ተደርጓል ያሉት አቶ ስንቁ ''በማኑፋክቸሪንግ የተሰማሩ ማህበራት ውጤታማ በመሆን ሽግግር እንዲያደርጉ በቂ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል'' ብለዋል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ባተኮረው የሦስት ቀናት ስልጠና የሶስቱም ዞን አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም