ቀጥታ፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከዳሽን ባንክ ጋር ተስማሙ

ኢዜአ ህዳር 25 /2012 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ዘመናዊ የትኬት ሽያጭ አገልግሎት ለመተግበር ከዳሽን ባንክ /አሞሌ/ ጋር ተስማምተዋል። ክለቦቹ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዲስ አበባን ወክለው የሚሳተፉ ብቸኛ ክለቦች መሆናቸው ይታወቃል። የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ ለ14 ጊዜ ባካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የስታዲየም መግቢያ ትኬቶችን በዳሽን ባንክ /አሞሌ/ ማከናወኑ ይታወሳል። ቀደም ሲል በፕሪሚየር ሊጉ ለሚደረጉ ጨዋታዎች ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ለመግባትና ጨዋታዎችን ለመከታተል ረዥም ሠዓት እንደሚሰለፉና ግርግርም ይፈጠርሩ እንደነበር ይታወቃል። ይህ የዳሽን ባንክ /አሞሌ/ የትኬት ሽያጭ ስርዓት ግን አሰራሩን ቀልጣፋና ለተመካቾችም አመቺ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር አመላክቷል። በስታዲየም በሮች ላይ ትኬት ለመቁረት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አላስፈላጊ ግርግሮችን በማስቀረት ረገድም ቁልፍ ሚና የሚጫወት ሆኗል። እናም ይህን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለቦች ከዳሽን ባንክ ጋር ስምምነት ፈጽመዋል። ክለቦቹ በፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብሮች በአዲስ አበባ ለሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የደጋፊዎች የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች ሙሉ በሙሉ በዳሽን አሞሌ የሚሸጡ መሆኑን አስታውቀዋል። በመሆኑም ደጋፊዎች ጨዋታዎችን ለመመልከት ወደ ስታዲየም በሚመጡበት ጊዜ ቀደም ብለው በዳሽን ባንክ በተመረጡ የአሞሌ ተቋማት ትኬት መቁረጥ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ክለቦቹ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶችን ዋጋም ይፋ ያደረጉ ሲሆን ከፍተኛው መግቢያ 300 ብር ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 20 ብር እንዲሆን መወሰናቸውንም ነው ያስታወቁት።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም