የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ ፕሮጀከት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ ፕሮጀከት ይፋ ሆነ
ኢዜአ ህዳር 25/2012 የአርብቶ አደሮችና የከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻልን ዓላማው ያደረገ ፕሮጀከት ዛሬ ይፋ ሆኗል። ፕሮጀክቱ በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች እየተተገበሩ ከሚገኙ መሰል ፕሮጀክቶች ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆንና የህብረተሰቡ ኑሮ በተጫባጭ እንዲለወጥ ጠንካራ የቅንጅት ስራ ያስፈልጋል ተብሏል። የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት /ኤል.ኤል.አር.ፒ/ን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ የሁለት ቀን አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ለስድስት ዓመት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት በስድስት ክልሎች በሚገኙ 100 ወረዳዎች የሚገኙ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል። በሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚተገበረው ፕሮጀክቱ 451 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል፤ በዋነኛነትም ሴቶችና ህጻናቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። የዓለም ባንክ ግሩፕና ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ /ኢፋድ/ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆነውን በጀት የሚሸፍኑ ይሆናል። የዓለም ባንክ ግሩፕ 350 ሚሊዮን ዶላር ድርሻውን ሲወስድ 70 ሚሊዮን ዶላሩ ድጋፍ፤ ቀሪው 280 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ነው። የተቀረውና በዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ የሚሸፈነው በጀት በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር እንደሆነ ተገልጿል። የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰይድ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን የግጦሽ መሬት መነሻ አድርጎ ኑሮውን የሚያሻሽል ነው። ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ከሆነበት የእንስሳት እርባታ በተጨማሪ በሌሎች መስኮችም በመሰማራት ገቢውን እንዲያሳድግ የሚያስችል ስራም በዋነኛነት ይሰራል። የመስኖ ልማት፣ የሰብል ምርት፣ የንብ ማነብና ልማት፣ የዶሮ እርባታ፣ የአፈርና ውሃ ሀብት ጥበቃና ሌሎችም ስራዎች በፕሮጀክቱ ይከናወናሉ ብለዋል። በክልሎቹ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በተቀናጀ መልኩ የማልማት፤ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን የምርት ስርዓት ማዘመንና የገበያ ተደራሽነታቸውን ማስፋትም ይጠቀሳል። ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮቹ የማህበራዊ አገልግሎትና የመሰረተ ልማት አቅርቦትን የማሻሻል ስራ ይሰራልም ነው ያሉት አቶ ሰይድ። ለዚህም ተቋማዊ አቅምን ማጎልበት፣ የእውቀትና የክህሎት ስልጠና መስጠት፣ የጥናትና ምርምርና ፖሊሲ ድጋፍ የማድረግ ተግባርም እንዲሁ። ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ማሻሻልና በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚደርስባቸውን ጉዳት እንዲቋቋሙ የማድረግ ግብ እንዳለውም ገልጸዋል። ቀደም ሲል ከእ.አ.አ 2003-2018 የአርብቶ አደሮች የልማት ፕሮጀክት /ፒሲዲፒ/ መተግበሩን አውስተው የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ ማህበራዊ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ነበር ብለዋል። 5 ሚሊዮን ዜጎች በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሆኑና የአሁኑ ፕሮጀክት ከቀደመው የሚለየው የግጦሽ መሬትን መነሻ አድርጎ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል ላይ ዋነኛ ትኩረቱን ማድረጉ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ ከሕዳር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑንና በ2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም ጠቁመዋል። የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን መንግስት አርብቶ አደሮችን ተቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን፤ የዛሬው ፕሮጀክትም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሩ ባለቤት ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በማቅረብ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል የሚያመቻች ነው ብለዋል። መንግስት ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግና የሚመለከታቸው አካላትም በጠንካራ ቅንጅት ከሰሩ ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ አመልክተዋል። የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ቢሮ የፕሮግራም መሪ ሚስ ናታሊያ ማይሌንኮ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ድርቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሰው ሰራሽ ችግሮች አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። ዛሬ ይፋ የሆነው ፕሮጀክት እነዚህ ዜጎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሱባቸውን ችግሮችና ጉዳቶች በመቋቋም ኑሯቸው እንዲሻሻል ከማድረግ አንጻር ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል። ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ክልሎች የስራ ሃላፊዎች የፕሮጀክቱ ጠቃሜታ የጎላ እንደሆነና ለተፈጻሚነቱም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በመንግስትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆን ማድረግና የአርብቶ አደሩንና የከፊል አርብቶ አደሩን እቅም ማጎልበት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ በአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል። የሠላም እና የግብርና ሚኒስቴሮች በፕሮጀክቱ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙ ሲሆን ስምምነቱ እስከ ታችኛው መዋቅር እንደሚቀጥል ተገልጿል። በፌዴራልና በክልል የፕሮጀክት ቁጥጥር ኮሚቴዎች የሚቋቋሙ ሲሆን ስራዎችን የሚገመግም የቴክኒክ ቡድን እንደሚቋቋምም ለማወቅ ተችሏል። ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት አውደ ጥናት የፌዴራልና መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው። በኢትዮጵያ 12 ሚሊዮን አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች እንደሚገኙ ከሠላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።