በመንገድ ትራፊክ አደጋ በየቀኑ 12 ሰዎች ይሞታሉ ---የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን

ህዳር 25/2012 የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ማስታወሻ ቀን "ሕይወት የተሽከርካሪ አካል አይደለም መለዋወጫ የለውም" በሚል መሪ ሃሳብ ሲታሰብ፤ በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በየቀኑ 12 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ ተባለ። 14ኛው የዓለም የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ማስታወሻ ቀን በኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ "ሕይወት የተሽከርካሪ አካል አይደለም መለዋወጫ የለውም" በሚል መሪ ሃሳብ በአቤት ሆስፒታል አዘጋጅነት ዛሬ በአዲስ አበባ ታስቦ ውሏል።

የመንገድ ትራፊክ አደጋ አስከፊነት በተለይም ባላደጉ አገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

የአደጋው ሰለባ ከሆኑት አገራት ጋር በምትመደበው ኢትዮጵያም በ2011 ዓ.ም ብቻ 4 ሺህ 597 ዜጎቿ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ለሕልፈት ተዳርገዋል።

ባለፉት ሶስት ወራትም በርካታ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋዎች ደርሰው በአዲስ አበባ ብቻ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መጎዳታቸውን የጤና ተቋማት መረጃዎች ያሳያሉ።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ አገሪቷ ካላት የተሽከርካሪ ቁጥር አንጻር እየደረሰ ያለው አደጋ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

የ2010 ዓ.ም የትራፊክ አደጋ ከ2011 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የቀነሰ ቢሆንም አሁንም በየቀኑ የ12 ሰዎች ሕይወት እየጠፋ ነው ብለዋል።

የትራፊክ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ ከታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበረው አሽከርካሪም ሆነ ተሳፋሪ ቀበቶ እንዲያስር የሚያስገድደውን ህግ ጠቅሰዋል።

የጤና ሚኒስቴር የድንገተኛና ጽኑ ሕክምና ዳይሬክተር ዶክተር አለኝታ ገብረእየሱስም የመንገድ ትራፊክ አደጋ በየጊዜው መጨመር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመግታት የሁሉም ዜጎች ርብርብ እንደሚያስፈልግም ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር መራጭ ዲንቄቻ በበኩላቸው በአሽከርካሪዎች ላይ የሚስተዋሉ የስነ-ምግባር ጉድለቶች ቢኖሩም የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀምም ችግር እንዳለበት ነው የተናገሩት።

አስከፊውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመከላከልና የአደጋ መጠኑን ለመቀነሰ በባለድርሻ አካላት ሰፊ እንቅስቀሴ እየተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተያዘው ወር የትራንስፖርት ሚኒስቴር "እንደርሳለን" በሚል መሪ ሃሳብ እየሰራ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት እ.አ.አ 2018 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለም ላይ በየ24 ሰከንድ አንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ሕይወቱን ያጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም