የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መቀዛቀዝ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት እንዲጨምር አድርጓል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መቀዛቀዝ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት እንዲጨምር አድርጓል ተባለ
ኢዜአ ህዳር 25/2012 የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መቀዛቀዝ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት እንዲጨምር ማድረጉን የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ዛሬ በበሽታው ስርጭት ዙሪያ ተወያይቷል። በውይይቱ የታደሙ የሃይማኖት አባቶች እንዳሉት፤ የበሽታው ስርጭት ሊጨምር የቻለው መዘናጋት በመታየቱ ነው። ቤተ እምነቶች ቀደም ሲል ሥርጭቱን ለመከላከል የሚሰጡትን ትምህርት አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል። መንግስት እና የሚመለከታቸው አጋር አካላት የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መጋቢ ሃይማኖት ቀሲስ አለሙ ሲራክ ጠቁመዋል። በከተማዋ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚሰሩ ጸያፍ ተግባራትን ለመከላከል የሁሉም ርብርብ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች እሴቶቻቸውንና ባህላቸውን መዘንጋት፣ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ ያለው የግንዛቤ እጥረት ለበሽታው ስርጭት ምክንያት እንደሆነም ነው የገለጹት፡ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል የሆኑት ሼህ ሰማን ሙሃመድ በበኩላቸው በመገናኛ ብዙሃን በኩል የኤችአይቪ/ኤድስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የአንድ ወቅት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ቤተ እምነቶች ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸው በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነኢየሱስ ቄስ ከበደ አበባው ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት የክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ታሪኩ ሞላ በአሁኑ ወቅት 59 በመቶ ሴቶችና 41 በመቶ ወንዶች ምንም አይነት ስለበሽታው ግንዛቤ እንደሌላቸው ተቋሙ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ገልጸዋል። በመሆኑም ሁሉም አጋር አካላት ርብርብ በማድረግ ስርጭቱን መቀነስ እንደሚገባ ተናግረዋል።