ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የወደፊት የልማት እድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ለሚመክረው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል

ኢዜአ ህዳር 25 / 2012 ዓም በኢትዮጵያ የወደፊት እድገትና ልማት እድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ለሚመክረውና በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ። በአውሮፓዊያን ቀመር 2050 የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አሁን ካለበት በእጥፍ በመጨመር 200 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመሆኑም አገሪቱ ይህንን ትንበያ መሰረት ያደረጉ ብሄራዊ የልማት ፖሊሲዎችንና እቅዶችን ከወዲሁ በመቀመር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባት የምጣኔ ኃብት ምሁራን ይመክራሉ።

ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን  የህዝብ ቁጥርንና የዜጎች ፍላጎትን እድገት ያጣጣመ ኃብት መፍጠር ያዳግታል፤ ይህም አገሪቱን ፈተና ላይ ሊጥላት ይችላል ሲሉም ያሳስባሉ።

"የ2050 የኢትዮጵያ እድሎችና ተግዳሮች ዓለም አቀፍ ጉባኤ" ዓላማም በመጪዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ  ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠር፤ ብሎም የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያግዙ የልማት አቅጣጫዎችን መጠቆም ነው።

በመጪው ታህሳስ 9 ቀን 2012 ዓም የሚጀመረውና ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መፍትሄ ጠቋሚ ጥናታዊ ጽሁፎችንና ሃሳቦችን ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤውን በትብብር ያዘጋጁት ኢትዮጵያ የምህንድስና ሙያ ማህበራት፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበርና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ተባባሪ አዘጋጅ መሆኑም ተመልክቷል።

በጉባኤው ላይ ከውጭ አገራትና ከአገር ውስጥ የተጋበዙ በጠቅላላው ከ300 በላይ ምሁራን፣ ባለሙያዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንደዚሁም የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከተሳታፊዎቹ መካከል ናቸው።

ተሳታፊዎቹም የውሃ ሃብት ልማትን፣ ትምህርትን፣ የሃይል አቅርቦትን፣ የምግብ ዋስትናን፣ ጤናን፣ ኢንዱስትሪን፣ መሰረተ ልማትንና የከተማ ልማትን ጨምሮ በአገሪቱ የወደፊት እድገት ላይ ሁነኛ ሚና ባላቸው ዘርፈ ብዙ የእድገትና የልማት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።

ጉባኤው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚጣጣም ምጣኔ ኃብት ለመገንባት የሚቻልባቸውን አቅጣጫዎችን ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአዘጋጆቹ መካከል የሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል ኢንጂነሮች ማህበር ፕሬዚደንት ኢንጂነር ተስፋዬ ወርቅነህ እንደገለጹት፤ ጉባኤውን እውን ለማድረግ ዓለም አቀፉ አደራጅ ኮሚቴና አራቱ የጋራ አስተናጋጆች ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

ጉባኤው አገሪቱ ሊኖራት የሚችለውን የሰውና ሌሎች ሃብቶችን መሰረት በማድረግ የተለያዩ አገራዊ ፍላጎቶችን ለማርካት በሚቻልባቸው እድሎች ላይ እንደሚመክር ኢንጂኒየር ተስፋዬ ገልፀዋል።

የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳው በበኩላቸው፤ በጉባኤው ላይ የሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሁፎችና የክርክር ሃሳቦች ጠቃሚ የፖሊሲ ግብአት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በተለይም መንግስት አሁን ላይ እያዘጋጀ ላለው የ10 ዓመት የልማት እቅድ የሚጠቅሙ ሀሳቦች ይቀርቡበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልፀዋል።

ጉባኤው ታላላቅ አገራዊ አጀንዳዎች የሚነሱበት በመሆኑ ወደፊት መንግስት በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ቀርፆ ለሚተገብራቸው ፖሊሲዎች የሚጠቅሙ የምሁራን ግብኣት በየጊዜው የሚቀርቡበትና በቋሚነት የሚካሄድ መድረግ ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋልም ሲሉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም