የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በነቀምቴ ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በነቀምቴ ተከበረ
ኢዜአ ህዳር 25/2012የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ትናንት በነቀምቴ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ። በዓሉ የፌደራሊዝም ስርዓትን በሚያጠናክር የዜጎችን አንድነት እንደሚያጎለብት አንዳንድ የበዓሉ ተሳታፍዎች ተናገሩ። በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ገመዳ ፍቃዱ እንደተናገሩት በዓሉ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመፈቃቀር የአንድነታችን እና የዴሞኪራሲ ስርዓት ግንባታ መገለጫ ነው ብሏል። ረዳት ፕሮፈሰሩ እንዳሉት በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንድ ጥላ ስር ሆነው ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን የሚያወድሱበት ቀን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር በኢትዮጵያ፣ ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውእንዲሁም በፌዴራሊዝም አስፈላጊነት ዙሪያ በረዳት ፕሮፈሰሩ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ አቶ ማሞ ኪትላ በሰጡት አስተያየት የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከባሉፉት ዓመታት ልዩ የሚያድረገው የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን መቀራረብ፣ መከባበርና መፈቃቀር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የፖርቲዎች ውህደት በተጀመረበት ማግስት መከበሩ ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት በዓሉ የአገሪቱን ህዝቦች አንድነት የበለጠ በማጠናከር አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሐረሰቦችና ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለሀገራቸው እድገትና ልማት በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል የገለፁት ደግሞ አቶ ተሰማ ሙለታ ናቸው። በዓሉ ፌዴራሊዝምን በማጠናከር የዴሞኪራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያጠናክር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ የነቀምቴ ከተማ አፌ ጉባኤ ወይዘሮ ሳድያ አህመድ እንደተናገሩት የተጀመረውን ለውጥ ቀጣይነት እንድኖረው ለማድረግ የብሔር ብሔረሰቦች አንድነትና መቻቻል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የለውጡ ቀጣይነትና የእድገትና ብልጽግና ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል። ''በዓሉን ስናከብር የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ፀረ ሰላም ሃይሎችን በአንድነት ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን በመግለጽ ነው'' ብለዋል፡፡