ቀጥታ፡

የአለም የሰብዓዊ መብት ቀን ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይከበራል

ኢዜአ፤ ህዳር 24/2012 የአለም የሰብዓዊ መብት ቀን ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ የሚከበር መሆኑን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል በአገር ውስጥ በሲቪል ማህበራት ተደራጅተው ከሚሰሩ ድርጀቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጿል። ‹‹ወጣትነት ለሰላም እና ለሰብዓዊ መብት መከበር›› በሚል መሪ ሐሳብ ለአምስት ቀናት የሚከበረውን የሰብዓዊ መብት ቀንን አስመልክቶ ኮሚሽኑ ከሲቪል ማህበራት ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የሰብዓዊ መብትን በተመለከተ በሚከበረው በዓል በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር ያሉ ተግዳሮቶች፣ ዕድሎችና ስኬቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የመወያያ ዕሁፎች እንደሚቀርቡ በመግለጫው ተጠቅሷል። የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሁም የሲቪል ማህበራት ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሰብዓዊ መብጥ ጥሰትን ለመከላከል መብትን ለማስከበር ከሚሰሩ ማህበራት ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተከሰተ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወጣቶች ከፖለቲከኞች የሚሰጣቸውን ግጭት ቀስቃሽ መልዕክት ብቻ በመከተል በሚፈፅሙት ተግባር  እንደሆነ ገልፀዋል። ኮሚሽኑ በቅርቡ ባደረገው  የማረሚያ ቤቶች ድንገተኛ ጉብኝት በታራሚዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሌለ ማረጋገጡን ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል። ''በተለያየ ጊዜ በተከሰቱ ግጭቶች ተሳታፊና ሰለባ የሆኑት ወጣቶች ናቸው'' ብለዋል። ወጣቶች ከዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለአገራቸው ሰላም መስራት እንዳለባቸው ዶክተር ዳንኤል መግለጫውን በሰጡበት ወቅት መልክታቸውን አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የመብት ጥሰት ለመከላከል የሁሉንም አካላት ትብብር የሚጠይቅ ስለሆነ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት እየተፈፀመ ያለው የመብት ጥሰትን ለመከላከል ከሚሰራው ስራ ባሻገር ፖለቲካዊ መፍትሄም እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። ሌሎችም በአገር ውስጥ የተደራጁ የሰብዓዊ መብትና በህግ ባለሙያ ማህበራት ሃላፊዎች በመግለጫው ተገኝተው በትብብር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም