የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ በተመለከተ የሚተላለፉ መልዕክቶች ግልጽ እንዲደረጉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ በተመለከተ የሚተላለፉ መልዕክቶች ግልጽ እንዲደረጉ ተጠየቀ
ኢዜአ ህዳር 24 ቀን 2012 የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ በተመለከተ የሚተላለፉ ሃይማኖታዊ መልዕክቶች ግልጽና ወጥነት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ። የሃይማኖት ተቋማት የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲጠፋ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ዘላቂነት ያለው የማስተማርና የማስገንዘብ ስራ መስራት እንደሚገባቸውም ተመልክቷል። የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የተዘጋጀው ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ለሃይማኖት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅና የ16ቱ ቀን የጸረ-ጾታ ጥቃት ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ የሃይማኖት ተቋማት የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ እንደሚከለክሉና እንደሚወገዙ ገልጸው፤ ነገር ግን የሚያስተላልፉት መልዕክት ወጥነት እንደሚጎለው ተናግረዋል። በእስልምና ሃይማኖት የሴት ልጅ ግርዛት ሃይማኖታዊ መሰረት 'አለው' እና 'የለውም' በሚል የተከፈለ ሀሳብ በመኖሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሰሩ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ለእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ደብዳቤ መጻፉንና የምክር ቤቱ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነ ወይዘሮ ስመኝ አስረድተዋል። በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን አስመልክቶ ያሉ አስተምህሮቶችና መልዕክቶች ግልጽ በሆነ መልኩ ለህብረተሰቡ ማስተማርና ማስገንዘብ እንዳለባቸው አመልክተዋል። የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቀር የሃይማኖት ተቋማት መደበኛ አስተምህሮታቸው ውስጥ በማካተት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ''በህግ መቅጣት ለውጥ ማምጣት አይችልም'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሰፊ ተከከታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በቅንጅት መሰራት እንዳለበት አክለዋል። በሚኒስቴሩ የተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ አምስት የማስፈጸሚያ ስልቶች ይዞ በነሐሴ 2011 ዓ.ም የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የተዘጋጀው ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ውስጥ የሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪያዎች ለቤተሰብና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር፣ ድርጊቱን የመቃወምና የወንዶች ተሳትፎ የመጨመር ሚና እንዳላቸው የሚገልጽ ሃሳብ መካተቱን ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ባላቸው ስፍራና ከፍተኛ ተደማጭነት አኳያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹ እንዳይፈጸሙ ቀድሞ የማስተማር መንፈሳዊና ሞራላዊ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። የሃይማኖት ተቋማት የጋራ አቋም በመያዝና በቅንጅት በመስራት የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን አስመልክቶ ያሉ አስተምህሮቶችን ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የድሬዳዋ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ አብደላ ሳኒ በእስልምና እምነት የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ሌሎች ሴት ልጅን የሚጎዱ ተግባራት መከልከላቸውን ገልጸዋል። ''ያም ቢሆን በሱና ሴት ልጅ ብትገረዝ ጥሩ ባትገረዘም አያስወቅሳትም የሚለውን ሀሳብ ይዘው መገረዝ ይፈቅዳል'' በሚል የእምነቱ አባቶች እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል። በእስልምና ሃይማኖት መርህ ውስጥ መጉዳትም ሆነ መጎዳት የተከለከለ እንደሆነ ገልጸው፤ ድርጊቱ እንዲቆም እንዲሁም አንድ የጋራ አቋም እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጉባኤው ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን በግልጽ እንደሚያወግዝና እንደሚቃወም ገልጸዋል። ጉባኤው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹም እንዲቀሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ያስችለው ዘንድ በ2008 ዓ.ም ግብረ ሃይል አቋቁሞ በክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል። ችግሩን ለማስወገድ ጉባኤው ከሰራው ይልቅ ያልሰራው እንደሚበዛና በዚህም ረገድ በቀጣይ ተከታታይነት ባለው መልኩ ስራዎችን በቅንጅትና በመናበብ እንደሚሰራም አመልክተዋል። ''በተጨማሪም የሃይማኖት ተቋማት የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለ እድሜ ጋብቻን የማስቆም ብሔራዊ ጥምረት ውስጥ አባል እንደሆኑና የተለያዩ የማስተማር ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛል'' ብለዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል።