ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻዎች አሏት -- የብሪታንያ ኩባንያዎች

ኢዜአ ህዳር 23/2012 ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻ የሆኑ በርካታ አማራጮች እንዳሏት በብሪታንያ የሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች ተወካዮች ገለጹ። ተወካዮቹ የኢትዮጵያ መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ እንዲረዱ የሚከውናቸው ሪፎርሞች በፍጥነት ገቢራዊ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል። በብሪታንያ የሚገኙ የተለያዩ ኩባንያ ተወካዮች ልዑክ በኢትዮጵያ ያለውን አማራጭ ለመቃኘት አዲስ አበባ ገብቷል። ልዑኩ "ኢንቨስት አፍሪካ" በተሰኘ የእንግሊዝ ድርጅት አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን ለሶስት ቀናትም ይቆያል። በዛሬ ውሎውም ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር መክሯል። መንግስትን ወክለው ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ኢትዮጵያና ብሪታንያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን የዳበረ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚው ሊያሰፉት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን ያሉ ድርጅቶች ለግሉ ሴክተር ክፍት መሆናቸውንም አብራርተዋል። እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በመጪው መጋቢት መጨረሻ ሁለት የግል ቴሌኮም ሴክተሮች ወደ ስራ እንደሚገቡ በመጠቆም። ኢዜአ ያነጋገራቸው የልዑኩ አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የተመቹ በርካታ አማራጮች እንዳሏት መገንዘባቸውን አውስተዋል። የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ንግድ መልዕክተኛ የነበሩት ጀርሜ ሊፍሮይ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በተለይ በኃይልና በግብርና ዘርፎች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ አላት። ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቁም እንስሳ አንጻርም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት በቀላሉ ለውጭ ንግድ ማቅረብ እንደሚቻል ጨምረው ተናግረዋል። የእንግሊዟ ንግስት የአፍሪካ ንግድ ምክትል ኮሚሽነር አልስቴር ሎንግ በበኩላቸው ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ግልጽ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ እንዳላት መገንዘባቸውን ገልጸዋል። ይህም ኢንቨስትመንቱን ለማስፋት ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቁመው፤ "የብሪታንያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ፍላጎት እንዲኖራቸው እንፈልጋለን" ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ስራን ቀላል ለማድረግ የጀመረውን ሪፎርም በፍጥነት ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባውም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከአስርት ዓመታት በላይ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት ለኢንቬስተሮች ትልቅ አቅም ነው ያሉት ደግሞ "የኢንቨስት አፍሪካ" ዋና ስራ አስፈጻሚ ካረን ቴለር ናቸው። የልዑካን ቡድኑ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በፋይናንስና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም መምጣቱንም ተናግረዋል። ነገር ግን የውጭ ምንዛሬና የገንዘብ ፍሰት ላይ ያሉ እንቅፋቶች በአፋጣኝ ሊወገዱ ይገባል ነው ያሉት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም