የአካል ጉዳተኞች ቀን እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞች ቀን እየተከበረ ነው
ህዳር 23/2012 የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በሻሸመኔ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡ በዓሉ ለ27ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው "የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና መሪነት በማጎልበት የ2030 የልማት አጀንዳን ውጤታማነት እናረጋግጣለን" ሚል መሪ ቃል ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሁሉም ክልሎች የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊዎችና የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዬች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ በበዓሉ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአካል ጉዳተኞችን እኩልነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል፡፡ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችን ያካተተና በሁሉም መስኮች ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት እየተሰራ ነው። በ2030 የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና መሪነት ለማረጋገጥ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡