ቀጥታ፡

በምርጫ አዘጋገብ ዙሪያ ለህትመትና ብሮድካስት ጋዜጠኞች የተዘጋጀ ስልጠና በአዳማ ተጀመረ

ኢዜአ ህዳር 23/2012 በሀገሪቱ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚዲያ አካላት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ። በምርጫ አዘጋገብ ዙሪያ ለህትመትና ብሮድካስት ጋዜጠኞች የተዘጋጀ የሶስት ቀናት ሥልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የባለሥልጣኑ ተወካይና የኮሙዪኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ወሳኝ ነው። ''ይህ እውን እንዲሆን የሚዲያ አካላት ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዘገባ ለህበረተሰቡ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል። በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ታሳቢ በማድረግ አቅማቸውን ለመገንባት ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። ማንኛውም ዲሞክራሳዊ ምርጫ የተለያዩ አላማና ፖሊሲ የያዙ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት መድረክ ስለሆነ ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከአድሎ የፀዳ መድረክ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። ስልጠናውን ባለስልጣኑ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ማእከል (ዩኔስኮ) በመተባበር ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ በበኩላቸው ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ወሳኝ ሚና ካላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል የመገናኛ ብዙሃን አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል። ስልጠናው በምርጫ አዘጋገብ፣ በምርጫ ወቅት ጋዜጠኞች መረጃ የማግኘት መብትና በሌሎችም ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። በሀገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ ሳይስተጓጐል በነፃነት፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ አኳኋን እንዲካሄድ በማሰብ ስልጠናውን በፋይናንስ መደገፋቸውን የተናገሩት ደግሞ በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አደራው ገነቱ ናቸው። የሚዲያ አካላት ተገቢው የውድድር ሜዳ እንዲፈጥሩ ከመነሻ እስከ መድረሻ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ዩኔስኮ ድጋፉን  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም