ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሴካፋ ውድድር አትሳተፍም - እግር ኳስ ፌዴሬሽን

ኢዜአ ህዳር 23 ቀን 2012 ኢትዮጵያ በመጪው ቅዳሜ በሚጀመረው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር /ሴካፋ/ እንደማትሳተፍ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ከሕዳር 27 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በዩጋንዳ በሚካሄደው ውድድር እንድትሳተፍ የምድብ ድልድል ውስጥ መካተቷ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከውድድሩ ከሚገኘው ጥቅምና ከሚወጣበት ወጪ አንጻር መሳተፉ አስፈላጊ አይደልም ብሏል።

የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንዳረጋገጡት ፌዴሬሽኑ ያለውን ውስን በጀት ለሴካፋ ውድድር ማዋሉ ጠቃሚ እንዳልሆነ ያምናል።

ከዚህም ባለፈ አንድ ውድድር የሚለካው በተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጥቅሞች ተገምግመው በመሆኑ በውድድሩ መሳተፉ ጠቃሚ አይደለም ብለዋል።

እናም ኢትዮጵያ በምድብ ድልድል ውስጥ የተካተተች ብትሆንም በውድድሩ አትሳተፍም ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም