በአፍሪካ ሰላምና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ለማምጣት የበይነ መንግስታት ግንኙነትን ማሳደግ ይገባለ ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሰላምና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ለማምጣት የበይነ መንግስታት ግንኙነትን ማሳደግ ይገባለ ተባለ
ኢዜአ ህዳር 22/2012 በኡጋንዳ ቆይታ ያደረገው የኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ልዑክ በአፍሪካዊያን መካከል ያለውን ዝቅተኛ የበይነ መንግስታት ግንኙነት ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው ልዑክ በአፍሪካዊያን መካከል አንድነት መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውጤታማ ቆይታ ማድረጉ ተገልጿል። በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዓለምጸሀይ መሰረት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የልዑካን ቡድኑ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ከባለሃብቶች፣ ከህዝብ ተወካዮችና የምርምር ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በኢትዮጵያና ኡጋንዳ መካከል ባለው ባለብዙ ወገን ግንኙነት፣ በኢጋድ፤ የአባይ ወንዝን ጨምሮ በጋራ ሃብት አጠቃቀም በትብብር ለመስራት ተወያይተዋል። በግብርና፣ በንግድና ቱሪዝም ዘርፎች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ውይይት ውጤታማ እንደነበርም ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ዋና የኢኮኖሚ መሰረታቸው ግብርና ቢሆንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው ዝቅተኛ ስለነበረ የእርስ በእርስ የንግድ ትስስራቸው አጥጋቢ አልነበረም ብለዋል። ኡጋንዳ ወደ ውጭ ከምትለከው ምርት 60 በመቶ የሚሆነውን ለጎረቤት አገራት እንደምታቀርብ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ተጠቃሚ አለመሆኗን ጠቁመዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በምትልከው ቆዳና ሌጦ፤ ኡጋንዳ በበኩሏ የወተት ምርቶችን በማቅረብ በጋራ ለመስራት ተወያይተዋል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያና ኡጋንዳ ባለፈ በበርካታ አፍሪካዊያን ዘንድ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ባደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና ተችሮታል። ከኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ልዑክ ጋር ውይይት ያደረጉት የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒም አፍሪካዊያን በትብብር የመስራት ልምዳቸው ውስን እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም አፍሪካዊያን በቀጣናው ሰላም ለማምጣትና ወደ ብልጽግና ጎዳና ለመጓዝ በቅድሚያ መተባበል እንዳለባቸው አሳስበዋል። በአፍሪካ የምርት ጥራት ችግር፣ ተመሳሳይ ምርት፣ የትራንስፖርት እጥረት ለበይነ መንግስታት ግንኙነት እንቅፋት እንደነበር የሚነገረው እንደመነሻ ተወስዶ ጥናት እንዲደረግም ተነጋገረዋል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ልዑካን ቡድን ከኡጋንዳው ማካሬሬ የጥናትና ምርምር ተቋም ጋር መምከራቸውን በመጠቆም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ነብያት ጌታቸው በበኩላቸው ለአምስት ቀናት የቆየው ልዑክ ውጤታማ ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል። የህዝቦችን አንድነት በማጎልበት የሁለቱን አገራት የዳበረ ግንኙነትና ትብብር ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።