ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በካይሮ እየተወያዩ ነው

ህዳር 22/2012 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በግብጽ ካይሮ እየመከሩ ነው። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ውይይት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የግብፁ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር ሞሐመድ አብደልና የሱዳኑ አቻቸው ፕሮፌሰር ያሰር አባስ እየተካፈሉ ነው። ውይይቱ የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሜሪካ ጋባዥነት በዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የሚካሄድ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ተናግረዋል። ህዳር 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የመጀመሪያው የሶስትዮሽ የቴክኒክ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል። በዋሽንግተን ዲሲ በተደረሰው ስምምነት መሰረትም አሜሪካና የዓለም ባንክ በውይይቶቹ በታዛቢነት እየተሳተፉ ይገኛሉ። የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ መኩሪያ ከአዲስ አበባው ውይይት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በካይሮ ለሚካሄደው ውይይት ሶስቱ አገሮች የሚመሩበት ሰነድ መዘጋጀቱንና ሰነዱም ውይይት እንደሚካሄድበት መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በአዲስ አበባ በተደረገው ውይይት በመስከረም 2012 ዓ.ም በካርቱም በተደረገው ስብሰባ የተለዩ ስድስት ነጥቦች ላይ መወያያታቸውን ገልጸዋል። አገራቱ ለውይይት ከቀረቡት ጉዳዮች ስምምነት የደረሱባቸው በአረንጓዴ መዝገብ እንዲመዘገብ እንዲሁም ስምምነት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች በቀይ መዝገብ እንዲመዘገብ መደረጉንም ተናግረዋል። አገራቱም በተስማሙባቸውና ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብሪያ ሰጥተው ውይይት እንደተደረገም ይታወቃል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በአዲስ አበባ በተደረገው ውይይት ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች የስምምነት ፊርማ መፈረማቸውም ይታወሳል። ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው የህዳሴ ግድብ ውይይት አገራቱ በግድቡ ዙሪያ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይተው ከስምምነት ላይ ለመድረስ የጊዜ ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል። የሶስቱ አገራት የውጭ ሚኒስትሮች ከቴክኒክ ስብሰባው በተጨማሪ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም እና ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በህዳሴ ግድቡ ላይ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ በመገኘት ስምምነቱ የደረሰበትን ለመገምገምና የውይይቱን ሂደት ለመደገፍ መስማማታቸውም ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ አፈጻጸም 69 ነጥብ 3 በመቶ ሲደርስ የሲቪል ምህንድስና ስራው ደግሞ 85 በመቶ ተጠናቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም