የኪነት ቡድኑ በአገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ላይ የቀረጻቸውን ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ተዘዋውሮ ለማቅረብ የተቋማትን እገዛ ይሻል - ኢዜአ አማርኛ
የኪነት ቡድኑ በአገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ላይ የቀረጻቸውን ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ተዘዋውሮ ለማቅረብ የተቋማትን እገዛ ይሻል
ኢዜአ ህዳር 22/2012 አንጋፋው የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን በአገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ላይ የቀረጻቸውን ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ተዘዋውሮ ለማቅረብ የተቋማት ተግባራዊ እገዛ ማጣቱን ገለጸ።
የወሎ የሀገር ባህል ተጫዋቾች ክበብ' በሚል ስያሜ በ1960ዎቹ ከ70 በላይ ባለሙያዎችን በማቀፍ የተመሰረተው አንጋፋው የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ማሪቱ ለገሰና ዘኒት ሙሃባውን ጨምሮ ዕውቅ ከያኒያንን አፍርቷል።
የኪነት ቡድኑ ለ22 ዓመታት ፈርሶ ቆይቶ 2006ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አማካኝነት ነባርና ወጣት አባላትን በመያዝ ዳግም ተመስርቷል።
አሁን ላይ ከ35 በላይ ድምጻዊያን፣ ተወዛዋዦችና ሙዘቀኞችን በማቀፍ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ስር ሆኖ እየሰራ ይገኛል።
የኪነት ቡድኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መላኩ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጸው ቡድኑ አሁን ላይ በአገራዊ አንድነት፣ በፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ላይ የራሱ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ ይገኛል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ የኪነት ቡድኑ የሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ብዝሃ ባህል እየተጫወተ ሲሆን ስራዎቹንም በክሊፕክ ማሳተም ጀምሯል።
የኪነት ቡድኑ በ1970ዎቹ መጀመሪያ "ፈጣኑ ባቡሩ" በተሰኘ ሙዚቃው ከወቅቱ ፕሬዝደንት ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መጓጓዣ መኪና ተበርክቶለት ነበር።
"የመደመር ባቡር" የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔት የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደግሞ ባለፈው ዓመት የመንቀሳቀሻ አውቶቡስ አበርክተውላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ዓመት ወደ ደሴ ባቀኑበት ወቅትም የቡድኑን ስራዎች ተመልክተው የኪነት ቡደኑ በመላ አገሪቷ ተዘዋውሮ አገራዊ አንድነትና ፍቅርን የሚሰበኩ ስራዎችን እንዲያቀርብ መጠየቃቸውንም ኃላፊው አስረድቷል።
በዚህም ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለኪነት ቡድኑ የኪነ ጥበብ ፕሮጀክት እገዛ እንዲያደርግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት አቅጣጫ ቢሰጠውም በጀት የለም የሚል ምላሽ መሰጠቱን ነው የተናገረው።
የኪነት ቡድኑ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተዘዋውሮ ስራዎችን ለማቅረብ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድጋፍ ደብዳቤ ተሰጥቶት ለዩኒቨርሲቲዎች ማመልከቱንም አብራርቷል።
በተለይም አገሪቷ አሁን ባለችበት ሁኔታ የኪነ ጥበባዊ ስራዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግልጽ፤ ቡድኑን ለመደገፍ መንግስታዊ ተቋማትና ባለሃብቶች ቃል ቢገቡም ተግባራዊ ምላሽ ግን አልሰጡንም ነው ያለው።
በሌላ በኩል አንዳንድ ዲፕሎማቶችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የስራ ሃላፊዎች የኪነት ቡድኑ ከአገር ውጭም ተዘዋውሮ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቁ ስራዎቹን ለማቅረብ ዕድል ለማመቻቸት ቃል መግባታቸውን ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ለኪነ ጥበቡ በመንግስት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠ ቢነገርም "በተግባር ግን አልተመነዘረም" ይላል።
ያም ሆኖ ግን የኪነት ቡድኑ የሌሎች ወገኖች ድጋፍ ቢያጣም በራሱ እየተንቀሳቀሰ ስራዎችን ለማቅረብ ተስፋ እንደማይቆርጥ አረጋግጧል።