ቀጥታ፡

በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛን መከላከል ላይ ያተኮረ ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ህዳር 22/2012 በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛን መከላከል አላማ ያደረገ ዓለም አቀፍ ስብሰባ በሚቀጥለው ሳምንት ታህሳስ 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት ይካሄዳል። "በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ: ዓለም አቀፍ ስጋት" በሚል መሪ ቃል ስብሰባው ይካሄዳል። ስብስባውን የአፍሪካ ህብረት፣ የእንግሊዝ መንግስትና በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛን መከላከል ላይ የሚሰራው የእንግሊዙ "ዊ ፕሮቴክት ግሎባል አሊያንስ" ተቋም በጋራ ያዘጋጁት ነው። የስብሰባው ዓላማ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛን መከላከል ላይ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት በድረ ገጹ አስፍሯል። በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረገው የህጻናት የወሲብ ብዝበዛ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስከተለ ያለው ጉዳትና በአፍሪካ ያለውን ስጋት አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል። "ህጻናት በዲጂታል ዘመን" እና "ቴክኖሎጂና አሁን የመጡ ስጋቶች" ውይይት ከሚደረግባቸው ርዕሶች መካከል ይገኙበታል። የቴክኖሎጂ እድገት፣ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረገውን የህጻናት የወሲብ ብዝበዛ ለመከላከል የህግ ማዕቀፎችና የህግ አስፈጻሚ አካላት እያከናወኑት ያለው ተግባር ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ናቸው። የአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረገው የህጻናት የወሲብ ብዝበዛ ለመከላከል ያዘጋጇቸውን እቅዶችም በስብበባው ላይ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። ፓለቲከኛ ያልሆኑ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ አስመልከቶ የተመደቡ አምባሳደሮች ጉዳዩን አስመለክቶ የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ ፕሪቲ ፓቴል፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት እና የ"ዊ ፕሮቴክት ግሎባል አሊያንስ" ሊቀመንበር ኤርኒ አለን በስብሰባው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በስብሰባው ላይ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይሳተፋሉ። "በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ህጻናትን ኢንተርኔት በመጠቀም ወዳልተገባ ወሲባዊ ድርጊት እንዲገቡና ለወሲብ ጥቃት ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረግ የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ ከሆኑና ዘመናዊ የሳይበር ወንጀሎች ተብለው ከሚጠቀሱ መካከል በዋንኛነት ይጠቀሳል። "ዊ ፕሮቴክት ግሎባል አሊያንስ" እንደገለጸው፤ የኢንተርኔት ትስስርና የሞባይል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ወሲባዊ ብዝባዛውን እያባባሰው መጥቷል። ባለፉት አስር ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የህግ አስፈጻሚ አካላት በመተባባር በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል። በበለጸጉና በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በተለይም የተንቀሳቃሽ ምስል ቴክኖሎጂ እድገትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የቁጥጥር ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም