ብልጽግና ፓርቲ መለያው እውነትና እውቀት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ መለያው እውነትና እውቀት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
ኢዜአ ህዳር 21/2012 ''ብልጽግና ፓርቲ መለያው እውነትና እውቀት የሆነና ኢትዮጵያን የሚያሸጋግራት ድልድይ ነው'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል ውሳኔ ያሳለፉ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል እና አጋር ድርጅቶች ዛሬ የስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል። ከፊርማው ስነ-ስርዓት በኋላ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደገለጹት፤ ኢህአዴግ በርካታ ጠንካራ ጎን የነበሩት ቢሆንም ደካማ ጎኑ እያመዘነ በጽኑ ህመም ውስጥ ገብቶ ነበር። ኢትዮጵያ ዜጎቿ ደስተኛ የሚሆኑባት አገር እንድትሆን የብልፅግና ፓርቲ ምኞትና ስሜትን በመቀነስ በእውቀትና በእውነት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። የኢህአዴግ አደረጃጀት ለውጥ ያስፈለገው በጽኑ የታመመ በመሆኑ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አብይ፤ ከውስጥ የለውጥ ሃሳብ ባይመጣ ኖሮ አገራዊ ኪሳራ ያጋጥም እንደነበርም አንስተዋል። ዘመኑን የሚመጥን አደረጃጀት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት የነበረው ሂደት ትክክለኛ እንደነበርም ተናግረዋል። በመሆኑም ፓርቲው ዴሞክራሲና ልማትን አጣምሮ የያዘ እንደሆነ አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረቱ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የሃሳብ ነጻነትን ማረጋገጥ ጭምር እንደሆነም አስገንዝበዋል። ፓርቲው የ10 አመት ዕቅድ ማዘጋጀቱን የገለጹት ዶክተር አብይ፤ ፕሮግራሙ ለህዝብ ተሰራጭቶ ውይይት የሚደረግበትና ከውይይቱ የሚገኙ ግብዓቶች የሚካተቱበት እንደሚሆን ጠቁመዋል። ብልጽግና ፓርቲ በህግና ደንብ የሚመራ እንዲሁም ህዝብን የሚጠቅም ሃሳብ ከማንኛውም ወገን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል። በፓርቲው የተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን ለመቀበል ዝግጁነት እንዳለም ጠቁመዋል። ብልፅግናን የተቀላቀሉት ፓርቲዎች ቁጥር ስምንት ደርሷል። ዛሬ የጋራ ስምምነቱን የተፈራረሙትም ውህደቱን ያጸደቁት ፓርቲዎች ሊቀ-መንበሮች ናቸው። በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።