ቀጥታ፡

በሀዋሳ 600 ሚለዮን ብር በሆነ ወጪ ዘመናዊ ሞል ሊገነባ ነው

ኢዜአ ህዳር 21/2012  በሀዋሳ ከተማ 600 ሚለዮን ብር በሆነ ወጪ መዝናኛና ሌሎችንም አገልግሎትችን በአንድ ማዕከል ያካተተ ዘመናዊ ሞል ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀመረ። ግንባታው የሚካሄደው በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ አትዮጵያዊንና ትውልደ አትዮጵውያን  "ውዘርን ጌት ኢንቨስትመንት " በሚል ስያሜ በመሰረቱት  አክሲዮን ማህበር  ሲሆን የግንባታው ስራም ትናንት በይፋ ተጀምሯል። በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈው ግንባታው  በሁለት ምዕራፎች ሆኖ በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው የታቀደው። የአክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ ዮሐንስ በወቅቱ እንዳሉት የጀመሩት ስራ  በሰው  ሀገር ጥረውና  ግረው ያገኙትን ገንዘብና እውቀት ወደ ሀገር ቤት በማምጣት የስራ እድል ለመፍጠርና የሀገሪቱን ልማት ለማገዝ  ነው። ማህበሩ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ርብርብ ሲያደርጉ መቆየታቸውን  አመልክተዋል። ቦታውን ከተረከቡ ከስድስት ዓመታት በላይ ቢሆናቸውም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደ ሥራ ስራ ሳይገቡ እንደቆዩ ጠቁመው የፕሮጀክቱ ሥራ እንዲጀመር  የክልሉ መንግስት ፣ የከተማዋ የማ አስተዳደሩና ሌሎችም አካላት ላደረጉት እገዛና ትብብር አመስግነዋል ፡፡ ሞሉ ሆቴል ፣ ካፌና ሬስቶራንት ፣ ለቢሮ አገልግሎት ሚውሉ ህንጻዎች፣ ሱቆች ፣ የሲኒማና የስብሰባ አዳራሾች እንዲሁም የአዋቂዎችና ሕፃናት መዝናኛዎችን በአንድ ማዕከል አካቶ የሚይዝ ነው። ከ250 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች  የሥራ ዕድል  ይፈጥራል ተብሏል። የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መልካሙ ወርቁ በበኩላቸው ሀዋሳ  ያላት የተፈጥሮ ፀጋ ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፣ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና የሞጆ ሀዋሳ ፍጥነት መንገድ ጨምሮ ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ እንዳደረጋት ተናግረዋል፡፡ ለከተማዋ እድገት የሚመጥኑ ዘመናዊ ገበያ ማዕከላትና ሆቴሎች እንደሚያስፈልጓት ገልፀው የሞሉ ግንባታ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት እንደሚሞላ ገልጸዋል፡፡ የሞሉ ግንባታ  ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ  የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ግንባታው ሲጀመር የተገኙት የኢፌዴሪ ዲያስፖራ ጉዳዮች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲስፖራ አቅም ቢኖራትም በዚህ ልክ አለመጠቀሟን ተናግረዋል ፡፡ "በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ያለውን የዲስፖራ አቅም ማስተባበር ቢቻል ከፍተኛ ሀብት ወደ ሀገሪቱ ማምጣት ሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው" ያሉት ወይዘሮ ሠላማዊት  የግንባታ ስራውን በይፋ የጀመረው ፕሮጀክትም ለዚህ ማሳያ እንደሆነ አስረድተዋል። መንግስት በተለይ ከለውጡ ወዲህ የዲያስፖራ ኤጀንሲን በማቋቋም  ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው የዘገዩ ፕሮጀክቶች እንዲቀጥሉ ጥረት እየተደረገ  መሆኑንም ገልጸዋል። የአክሲዮን ማህበሩ አባላት ፣ የፌዴራል ፣ የደቡብ ክልል፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሞሉ ግንባታ ማስጀመሪያ ስነሰርዓት  ተገኝተዋል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም