ኢትዮጵያና ቻይና በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቻይና በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
ኢዜአ ህዳር 21/2012 ኢትዮጵያና ቻይና በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ ስምምነት አደረጉ። ኢትዮጵያና ቻይና በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ አነስተኛና መካካለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ለማጎልበት ያለመ ስምምነት ትናንት መደረጉን የቻይና የዜና ምንጭ (ዥኑዋ) በዘገባው አስፍሯል። የመግባቢያ ሰነዱ በኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተኬ ገብረእየሱስና በቻይና የኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዋንግ ጂአንግፒንግ አማካኝነት ነው የተፈረመው። የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የትብብር ስምምነቱን አገሮች በዘርፉ አብረው ለመስራት ያግዛቸዋል። ዳይሬክተሩ ጨምረውም ስምምነቱ በኢትዮጵያና ቻይና ኢንተርፕራይዞች መካከል የማምረቻ ጥሬ እቃዎችን በመለዋወጥ ትስስር ለመፍጠር ይረዳልም ብለዋል። በተጨማሪም በሁለቱ አገሮች አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች መካከል የገበያ ትስስር እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት። ቻይና ዘርፉን በማሳደግና በማልማቱም ያላትን ልምድ በመገንዘብ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሊማሩት የሚችል በርካታ ተሞክሮ መኖሩን በአጽእኖት አንስተዋል። ኢትዮጵያ ከቻይናው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አሊባባ ቡድን መስራች ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ስምምነት ማድረጓን ዥኑዋ በመረጃው አስታውሷል።