ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ የድል ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ይገኛል ... አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ኢዜአ፤ ህዳር 20/2012 የጋምቤላ ብሄራዊ ክልል አገራዊ ለውጡ በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ወደ አዲስ የድል ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

''ህገ- መንግስታዊ ቃል ኪዳናቸን ለዘላቂ ሰላም'' በሚል መሪ ሀሳብ 14ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በክልል ደረጃ ላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ በክብር በዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ በተፈጠረው አገራዊ ለውጥ ክልሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የክልሉ ህዝብ በአገሩ ጉዳይ የመወሰን መብት እንዲኖረው ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ጥያቄው ምላሽ ማግኘት በመቻሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ የተደረገው የኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች ውህደት የክልሉ ህዝብ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል የመወሰን መብታቸውን እንደሚያረጋግጥ ጠቁመው፤ ይህም ከወንድማማች ህዝቦች ጋር ያለውን አንድነትና አብሮነት በማጠናከ ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ ህዝብ ለተጀመረው ክልላዊና አገራዊ የለውጥ ስኬት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ጠንክሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ህዝቡ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቹን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በጋራ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መሰተዳድሩ አቶ ኡሞድ፤ ህዝቡ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቹን በማጠናከር በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደፊት ለማራመድ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ ላክደር ላክባክ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የክልሉ ህዝብ ህገ መንግስቱ ከጸደቀበት ማግስት ጀምሮ ራሱን በራሱ በማስተዳደር የበርካታ ድሎች ባለቤት ሆኗል።

በቅርቡ አንድ ህብር ብሄራዊ ፓርቲ በመመስረቱ የአግላይነት ስህተቶችን በማረም የህዝቦችን እኩል የመወሰን የዜግነት መብትና አቃፊነትን የሚያረጋጥ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ስለሆነም ህዝቡ በክልሉ ያለውን ሰላም ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወደ ፊት ለማሻገር በትጋት መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።

የዘንድሮን የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ሲከበር እውነተኛ የፌዴራዝም ስርዓት በመገንባት እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከግብ ለማድረስ በማለም እንደሆነም አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ ትሁት ሐዋሪያት በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ በዓሉን ያከበሩት አንድነታቸውን፣ አብሮነታቸውንና ሰላማቸውን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ነው።

“የሴቶች መብት የተከበረውና እኩል የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ተጠቀሚነታቸው እውን የሆነው ህዳር 29 በጸደቀው ህገ- መንግስት ነው” ያሉት ደግሞ ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ አቻላ ኡጁሉ ናቸው።

በዓሉ በባህላዊ ትሪትና ሌሎች ዝግጅቶች በክልል ደረጃ በላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ ተከብሮ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም