የሶዴፓ ጉባዔ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሶዴፓ ጉባዔ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ
ኢዜአ ህዳር 20/ 2012 የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) ዛሬ ባካሄደው ጉባዔ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቆታል። ፓርቲው ድርጅታዊ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል። በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ የሶዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና ማእከላዊ ኮሚቴ ቀደም ብሎ የብልጽግና ፓርቲን ለመዋሃድ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ከመከረ በኋላ ነው የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ባብላጫ ድምጽ ያጸደቀው። የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤው ከተገኙ 745 አባላት መካከል በአንድ ድምፅ ተቃውሞ እና በአንድ ድምጽ ተአቅቦ ውህደቱን በአብላጫ ድምፅ ነው ዛሬ ያጸደቀው። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል እና አጋር ድርጅት የሆኑ ፓርቲዎች ብልፅግና ፓርቲን ለመቀላቀል በጉባዔያቸው ውሳኔ ያሳለፉ ድርጅቶች ቁጥር ስምንት መድረሱ ታውቋል።