በደሴ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግር ወጣቱን ለሱስ እያጋለጠ ነው---የከተማዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግር ወጣቱን ለሱስ እያጋለጠ ነው---የከተማዋ ነዋሪዎች
ደሴ ኢዜአ ህዳር 20 2012---በደሴ ከተማ በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እጥረት ምክንያት ወጣቱ ለሱስ እየተጋለጠ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ። ከህብረተሰቡ የተነሳው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ያመነው የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። 22ኛው የደሴ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ተካሂዷል። የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱራህማን አሊ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው እደገለጹት በከተማው በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ባለመኖሩ ወጣቶች ለተለያዩ ሱሶች እየተጋለጡ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜ የሱስ ተጠቂ በመሆናቸው ተስፋ ከመቁረጥ ባለፈ ለጸጥታ ችግር ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል። ወጣቶቹ በመጤ ባህል ተጠምደው የኢትዮጵያ ባህልና እሴት እንዲሸረሸር ምክንያት እየሆኑም ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። መንግስት በየቀበሌው በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት ጤነኛ፣ አምራችና አገር ተረካቢ ዜጋ የማፍራት ግዴታውን እንዲወጣም ነው አቶ አብዱራህማን የጠየቁት። ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ እንግዳወርቅ ካሳሁን በበኩላቸው በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታና ስታዲየም አለመኖር ወጣቶች በስፖርቱ ተወዳዳሪ በመሆን የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እንዳይነሳሱ ማድረጉን ገልጸዋል። ወጣቶቹ በመንገድ ላይ ስፖርት ለመስራት ቢሞክሩም ለትራፊክ አደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታ ስላለ ህብረተሰቡን በማስተባበር ምቹ የስፖርት ማዘውተሪ ያቦታ እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው በበኩላቸው "ህብረተሰቡ የሚያነሳውን ችግር ለመፍታት ቢያንስ 26 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ እንደሚስፈልጉ በጥናት ተለይቷል" ብለዋል። እስካሁን በተካሄደ እንቅስቃሴ ስምንት የስፖትርት ማዘውትሪያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት ለወጣቱ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። ቀሪ 18 ማዘወተሪያ ቦታዎችን ለማመቻቸት በተለያዩ ቀበሌዎች ያሉ ከፍት ቦታዎች መለየታቸውንም አቶ ሰይድ ጠቁመዋል። አቶ ሰይድ እንዳሉት የተለዩ ቦታዎችን ከሦስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ ለማልማት እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በ223 ሚሊዮን ብር ከ25ሺህ በላይ ሰዎችን የሚይዝ ዘመናዊ ስታዲየም በከተማዋ ለመገንባት ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል በበኩላቸው "ለማልማት የታቀዱ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታች በታቀደላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ከተማ አስተዳደሩ የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል፡፡ ወጣቱ ከሱሰኝነትና አልባሌ ቦታ ከመዋል ተቆጥቦ በባህላዊና ዘመናዊ ስፖርቶች እየተሳተፈ ደሴ ከተማ እንዲያስጠራም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። ስፖርቱን ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዲያድግ ለማድረግም ከባለሃብቱንና በውጭ አገራት የሚኖሩ የከተማ ተዋላጆችን በማሳተፍ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በጉባኤው ለተለያዩ ተግባራት የሚውል ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የጸደቀ ሲሆን ለዘርፉ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የመስጋናና የእውቅና ሽልማት መሰጠቱ ተመልክቷል።