የእናት ባንክ አጠቃላይ ሀብት 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
የእናት ባንክ አጠቃላይ ሀብት 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደረሰ

ኢዜአ ህዳር 20 ቀን 2012 የእናት ባንክ አክሲዮን ማህበር የ2011 በጀት ዓመት አጠቃላይ ሀብት 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ።
ባንኩ 234 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ያገኘ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት የ18 ሚሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል።
ባንኩ 6ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ አካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን ባለፈው ዓመት ከነበረው ብር 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን የ43 በመቶ ዕድገት በማሣየት ብር 7 ነጥብ 12 ቢሊዮን ደርሷል።
የእናት ባንክ አክሲዮን ማህበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሐና ጥላሁን በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ባንኩ ባለፉት ዓመታት በአማካይ የ38 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን አጠቃላይ ሃብቱ 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ከባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ የ48 በመቶ ድርሻ የያዘው የቁጠባ ሂሳብ ሲሆን የጊዜ ገደብ ተቀማጭ እና የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ደግሞ የ40 በመቶ እና የ12 በመቶ ድርሻ ይዘዋል።
እንደ ወይዘሮ ሐና ገለጻ፤ ባንኩ በህዝብ ዘንድ ያተረፈው ተዓማኒነትና ሀብትን ለማሳደግ የተከተላቸው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች ውጤታማ መሆናቸውን ያመላክታል።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ የገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን 56 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።
እንዲሁም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያበደረው ጠቅላላ የብድር መጠን 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ወይም የ54 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ፕሬዚዳንቷ አብራርተዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ የብድር አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ብድር ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ ለኮንስትራክሽን 20 በመቶ፣ ለወጪ ንግድ 21 በመቶ፣ ለገቢ ንግድ እና ለአገር ውስጥ ንግድ ለእያንዳንዳቸው 17 በመቶ ተጠቃሽ ናቸው።
በተጨማሪም ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለትራንስፖርትና ለሌሎች የንግድ ዘርፎች የ25 በመቶ ብድር ባንኩ መስጠቱን ወይዘሮ ሐና አብራርተዋል።
የባንኩ አጠቃላይ ብድር መጠን ከተቀማጭ ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር 72 በመቶ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ ባንኩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ቢል መግዛቱን ተናግረዋል።
ባንኩ የሰጣቸውን ብድሮች ጤናማነት በየጊዜው በሚያደርገው ክትትል የተበላሹ ብድሮች ከጠቅላላው ብድር መጠን ጋር ያላቸው ጥመርታ ከሁለት በመቶ በታች ማድረግ እንደተቻለም አስረድተዋል።
''በአጠቃላይ ባንኩ በ2011 ዓ.ም ያለውን ሀብት በአግባቡ እየተጠቀመ መሆኑን የሚያሳይ ነበር'' ብለዋል።
በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 1 ነጥብ 2 ብር የደረሰ ሲሆን የባለአክሲዮኖች ብዛት ደግሞ ከ17 ሺህ በላይ ደርሷል፤ የሴቶች ድርሻ በቁጥር 64 በመቶ ሲሆን በካፒታል መጠን ደግሞ 59 ከመቶ ነው።
እናት ባንክ የሴቶችን የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ የብድር መያዣ ማቅረብ ለማይችሉ ሴቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች በማዘጋጀት ከባንኩ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
በ2011 በጀት ዓመት የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑ 8 ተበዳሪ ሴቶች የወሰዱትን ብድር በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ከፍለው በማጠናቀቅ 173 አዳዲስ የስራ ዕድል በመፍጠር ንብረት ማፍራት ችለዋል።
ባንኩ በንግድ ሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን በገንዘብ ለማገዝ በሚሰጠው ልዩ ትኩረት በበጀት ዓመቱ ካበደረው አጠቃላይ የብድር መጠን ውስጥ 933 ሚሊዮን ብር ለ714 በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
እንዲሁም ባንኩ ለሁለት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የሰጠውን ብድር ወደ 10 ሚሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን በአጠቃላይ 991 ሴቶች የብድር ተጠቃሚ ሆነዋል።