ግንባሩ ዘንድሮ ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ግንባሩ ዘንድሮ ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ጠየቀ
ኢዜአ ህዳር 20 ቀን 2012 የኢትዮጵያ አንድነት ብሔራዊ ግንባር ዘንድሮ ለማካሄድ የታቀደው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ጠየቀ። በአገሪቷ እየታዩ ያሉ ችግሮችን መፍታትና የሕግ የበላይነት ማስፈን ካልተቻለ ምርጫው መካሔድ አለበት ብሎ እንደማያምን ግንባሩ አስታውቋል። የግንባሩ አስተባባሪ ኮሚቴዎች የአገሪቷን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክተው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫውን ማካሔድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች የሉም። የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ አንዷለም ጥላሁን ሠላምና መረጋጋት ባልሰፈነበት፣ የዜጎች ደሕንነት ባልተጠበቀበትና የሕዝብ ቆጠራ ባልተካሔደበት ሁኔታ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊካሔድ ይችላል የሚል እምነት የለንም ብለዋል። በመሆኑም ምርጫው ከመካሔዱ በፊት የአገርና የዜጎች ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንዲቀድምና መጪው አገራዊ ምርጫ ሁሉም ወገን ለሚስማማበት ጊዜ እንዲራዘም ጥሪ አቅርበዋል። ጎን ለጎንም መንግስት በአገሪቷ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ የዜጎች ሠላምና ደህንነት እንዲጠበቅ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን ብለዋል። የግንባሩ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አስካለ ኃይሌ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ለብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ አንድነት ብሔራዊ ግንባር የአስር ፓርቲዎች ጥምረት መሆኑም ተገልጿል።