ቀጥታ፡

አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሰላምና መረጋጋትን ቅድሚያ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ

 ኢዜአ ህዳር 20 ቀን 2012 አገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቅድሚያ በየደረጃው ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ተናገሩ።

በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው 14ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ዘንድሮ “ህገ-መንግስታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ በየደረጃው ሰላምን በሚያረጋግጡ የውይይት መድረኮች ይከበራል።

ባለፉት ዓመታት ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸው በህገ-መንግሰቱ እውቅና እንደተሰጠውና ቋንቋና ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ለማንነታቸው መከበር የተሰጠውን ትኩረት ያህል አገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን በማስረፅ በኩል ውሱንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

"አገራዊ ለውጡን ተክትሎ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ፍቅርንና አብሮነትን በሚያጎላ መልኩ ትውልዱን  ለመቅረጽና ለማነጽ በዓሉ ወሳኝነት ይኖረዋል" ብለዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ተቻችለው፣ ተፈቃቅረውና  በጋራ ተጋምዶ  ለመኖር የሚያስችል ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥ በሚረዱ የውይይት መድረኮች በዓሉን ማክበር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

"የአማራ ክልል ህገ-መንግስት አቃፊ ሆኖ በመቀረጹ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች በልዩ ዞንና ወረዳ ተዋቅረው እራሳቸውን በራሰቸው እንዲያስተዳድሩ በማድረጉ በአገር ደረጃ ሞዴል ያደርገዋል" ብለዋል።

ለኦሮሞ፣ አዊ ፣ ዋግህምራና አርጎባ ብሔረሰቦች ዕውቅና የሰጠና ከአማራው ብሔረሰብ ጋር በጋራ ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ እንዲኖሩ ማድረጉን ተናግረዋል።

በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እንደመጤ የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው ይህን አመለካከት በቀጣይ ለመቅረፍ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

"የአማራ ክልል ህዝብ የትም ቦታ ሁሉ ቤቴ፣ ሁሉ ዘመዴ ብሎ ነው የሚኖረው" ያሉት ወይዘሮ ወርቅሰሙ "ይህ አብሮነት ለአገራዊ አንድነት መሰረት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል" ብለዋል።

አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ለአማራም ሆነ ለሌሎች ክልል ህዝቦች በእኩልነት አብሮ ለመኖርና በፍትሃዊነት ለመጠቀም የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅሬ ሙሉጌታ በበኩላቸው ዘንድሮ 14ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት "ህገ-መንግስታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ልማታችን” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ከተማ በሚከበረው በእዚህ በዓል ላይ ከክልሉ የሚሳተፉ 114 የባህል ቡድን፣ የሲፖዚየም ተሳታፊና የባዛር ተሳተፊ ኢንተርፕራይዞች  ያካተተ ቡድን መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም