ቀጥታ፡

ሰላምን ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ ሊደግፍ ይገባል

(ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2012 ሰላምን የማስጠበቅና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ችግሩን መግታት እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የህዝቦችን ለዘመናት የዘለቀ አብሮነትና መፈቃቀር ለማፈረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ህዝቡ አጋልጦ በመስጠት ትብብሩን እንዲያሳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት አሁን ኢትዮጵያ የገጠማትን ዘርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት ማስቆም የሚቻለው ህዝቡ ከመንግስት ጎን መሰለፍ ሲችል ነው።

ከህዝቡ ስነ ምግባር ጋር አብሮ የማይሄድ ዘርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭትና ብጥብጥ ኢትዮጵያ በታሪኳ አጋጥሟት እንደማያውቅ ገልጸዋል።

"በየአካባቢው የሚነሳው ግጭትም የበርካታ ንጹሀን ዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ አካልን በማጉደልና ንብረት በማውደም እያስከተለ ያለው ችግር አገርና ህዝብን እየጎዳ ነው" ብለዋል።

እንደሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጻ ይህን ችግር በአጭሩ መግታት የሚቻለው መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ህዝቡ በመተባበርና ማገዝ ሲችል ብቻ ነው።

ሃይማኖትና ዘርን መሰረት በማድረግ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ኃይሎችን ከመንግስት ይልቅ ህዝቡ ጠንቅቆ ስለሚያውቃቸው ነቀሶ በማውጣት በህግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመቻቻልና አብሮ በመኖር ለአልም ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያ ዛሬ የዓለም መሳለቂያ ሊያደርጓት የተነሱ የጥፋት ኃይሎች ኢትዮጵያዊያንን የማይወክሉና ሊወገዙ የሚገባ መሆኑንም ገልጸዋል።

"የየትኛውም የሃይማኖት ተቋም እርስ በእርስ የሚያጋጭ አስተምህሮት የለውም" ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ፣ ቅዱሳት መጻህፍትም ይህንን መጥፎ ድርጊት እንደማይቀበሉ ለህዝቡ የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ህዝቡን እርስ በርስ ሊያጋጩ የተነሱ አካላት በምዕመኑ ዘንድ ቦታ እንዳያገኙ የሃይማኖት ተቋማት በአስተምህሮታቸው አካተው ለማስገንዘብ ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭትና ሁከት በህዝቡ ላይ ግራ መጋባትና ጭንቀት መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሰዒድ መሀመድ ናቸው።

"በኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያን የሃይማኖትና የዘር ልዩነት ሳይገድባቸው ተጋብተውና ተዋልደው፤ በፍቅርና በመተሳሰብ በሚኖሩባት አገር የእርስ በርስ ግጭት መነሳቱ መሰረት የለውም" ብለዋል።

የፖለቲካ ቁማርተኞች ለግል ፍላጎታቸውና ጥቅማቸው ሲሉ ዘርንና ሃይማኖትን ምክንያት በማድረግ በሚፈጥሩት ግጭት የንጹሀን ደም መፍሰሱ በሰማይም ሆነ በምድር እንደሚያስጠይቃቸው ተናግረዋል።

የሚፈጠረውን አገራዊና አካባቢያዊ ችግሮች ለመከላከል በአስተምህሮቶቻቸው የምዕመኑን አስተሳሰብና አመለካከት በመለወጥ ከመንግስት ጎን እንደሚሰለፉ አስገንዝበዋል።

ችግሩን በእንጭጩ ለማስቀረት ህዝቡ  ዘር፣ ሃይማኖትና ጎጠኝነት ላይ ሳይሆን እንደ አባቶቹ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጋራ መቆም ይኖርበታል።

እንደአገር ኢትዮጵያን አሁን የገጠማት ፈተና በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅና አስነዋሪ ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል ታየ ናቸው።

"ባለፉት ዘመናት የኃይል የበላይነትን ለማሳየት የእርስ በርስ ግጭቶች ቢኖሩም እንደዛሬው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥላቻ አልነበረም" ብለዋል።

እየተፈጸሙ ያሉ ደርጊቶች የእምነት አባቶችን ያሳፈረና እንባ አውጥተው እንዲያለቀሱ ያስገደደ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

"የሰው ልጅ የፈለገውን ሃይማኖት እንዲከተል ነጻነት የተሰጠው ፍጡር ሁኖ እያለ በሃይማኖት ስም ሀይማኖቱን የማይወክሉ አካላት ህዝቡን እርስ በርስ እንዲባላ እያደረጉት ነው" ብለዋል።

ህዝቡ ለኢትዮጵያዊያን እንግዳና መጥፎ የሆነ ድርጊት አንድነቱን በማጠናከር ሊከላከለው እንደሚገበ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም