ወጣትነትን ለጥፋት ሳይሆን ለልማት በማዋል የኢትዮጵያ አንድነትን ማጎልበት ይገባል...የሃዋሳ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣትነትን ለጥፋት ሳይሆን ለልማት በማዋል የኢትዮጵያ አንድነትን ማጎልበት ይገባል...የሃዋሳ ከተማ ወጣቶች
ሃዋሳ ሰኔ 14/2010 ወጣትነትን ለጥፋት ሳይሆን ለልማት በማዋል የኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ በሃዋሳ የተፈናቀሉ ወገኖችን በማገልገል ላይ ያሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገለጹ፡፡ በሃዋሳ ከተማ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው ግጭት በርካታ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተዘጋጁላቸው ጊዜዊ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከመጠለያዎቹ አንዱ በሆነው ታቦር አንደኛ ድረጃ ትምህር ቤት ቅጥር ግቢ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያከናወኑ ካሉ ወጣቶች መካከል የኢትዮ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሰልጣኝ ወጣት የኔነህ ቸርነት አንዱ ነው፡፡ እሱን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የተሰባሰቡት ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ሲሆን ያሰበሰባቸውም ኢትዮጵያዊነት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ ኮሚቴ አዋቅረው ከሕብረተሰቡ ያሰባሰቡትን ድጋፍ ለተፈናቃዮች በማድረስና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማከናወን ጊዜያቸውን ከተፈናቃዮቹ ጋር በማሳለፍ ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ "ወጣትነት የልማት ኃይል ነው" ያለው ወጣቱ፣ ብሔርተኝነትን በማስወገድ በህዝቦች መካከል የነበረውን አብሮ የመኖር ባህል እንዲመለስ ሕብረተሰቡን ለማስተማር መዘጋጀታቸውን ተናግሯል፡፡ ሌላኛው በጎ ፈቃደኛ ወጣት አቡሌ አሸንጎ እንደገለጸው ተፈናቃዮችን መርዳት የጀመሩት ከአካባቢው ባሰባሰቡት የእለት ምግብ መሆኑንና ያሰባሰባቸውም ሰብአዊነት መሆኑን ተናግሯል፡፡ የተከሰተው ግጭት ተገቢ ያልሆነና ዘመኑን የማይገልጽ ቢሆንም አካባቢው ወደቀደመ ሰላም ሲመለስ አንድ ህዝቦች እንደምንሆን በመገንዘብ ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለአገር መስራት እንደሚገባ አመልክቷል። "ሰው በፍቅር ሲኖር ሃገር ማሳደግ ይችላል" ያለው ወጣቱ ማንም ሰው ዘሩን መርጦ አለመወለዱንና በዚህ ምክንያት ደም መፋሰስና ሕይወት ማጣት አግባብ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ "መሰባሰባችን ተፈናቃዮችን ከማጽናናት ባለፈ ወጣትነት ለጥፋት ሳይሆን ለልማት ሲውል ለውጥ እንደሚያመጣ በመገንዘባችብን ነው" ብሏል፡፡ በበጎ ፈቃድ በተሰባሰቡበት የተፈናቃዮች መጠለያ ሥፍራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተው መጎብኘታቸው እንዳስደሰተው የገለጸው ደግሞ ሌላኛው የሃዋሳ ከተማ ወጣት ለገሰ ተመስገን ነው፡፡ " በማደግ ላይ ያለች አገር ይዘን ወጣትነትንና ትምህርታችንን ለጥፋት መሳሪያነት ከምናውል ለልማት ልንጠቀም ይገባል፤ የትንሿ ኢትዮጵያ ምሳሌ የሆነችውን ሃዋሳን ወደ ቀደመ ስሟ መመለስ የወጣቱ ድርሻ ነው" ብሏል። "ሰው በመሆኔ በበጎ ፈቃድ ተፈናቃዮችን እየረዳሁ ነው" ያለው ወጣት ሙሉቀን ጠብቄ በበኩሉ የማንተዋወቅ ወጣቶች በምናውቀው ችግር ተሰባስበናል ብሏል፡፡ ወጣቱ ላልተፈለገ ተግባር መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት ያለው ወጣቱ፣ ወጣትነትን ከጥፋት ይልቅ ለልማት በማዋል የኢትዮጵያ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግሯል። የታቦር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሰመረ ኃይሉ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ከ1 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መጠለላቸውንና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መልካም ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል። የትምህርት ተቋማት በጥፋትም በበጎ ተግባርም የሚሰማሩ ዜጎችን በማፍራት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ "ሞራል ያለውና ሰብአዊነት የሚሰማው ትውልድ የመፍጠር ኃላፊነታችንን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡