የኤሌክትሪክ መስመር አለመዘርጋት በአዋሽ-ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ መስመር አለመዘርጋት በአዋሽ-ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው
ደሴ (ኢዜአ) ህዳር 20 ቀን 2012 ከአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የምድር ባቡር መስመር ግንባታ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም የኤሌክትሪክ መስመር አለመዘርጋቱ ችግር እንደፈጠረባቸው የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
የባቡር መስመር ግንባታ ሥራው የገጠመውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ ችግር በቅርብ ጊዜ ውስጥ በመነጋገር እንደሚፈታ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገልጸዋል።
የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም ተጀምሮ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ስምምነት ተፈጽሞ ነው ወደሥራ የተገባው።
በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የተገነባውና 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት 10 ጣቢያዎች፣ 51 ድልድዮች፣ 12 ዋሻዎችና ሌሎች የተያያዥ ሥራዎችን ያካተተ ነው።
"ከአዋሽ - ኮምቦልቻ ያለው መንገድ 99 በመቶ እንዲሁም ከኮምቦልቻ ሃራ ገበያ ያለው 70 በመቶ ቢጠናቀቅም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦች ችግር የሙከራ ጉዞ ማድረግ አልቻልንም" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሙከራው ተጠናቆ የባቡር መስመሩ ሙሉ በሙሉ ሥራ የሚጀምርበት ወቅት ቢሆንም በገጠመው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያት ኩባንያቸው ለኪሳራ እየተዳረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ስምንት የኤሌክትሪክ ኃይል መቀበያና ማሰራጫ ጣቢያዎችን በ250 ሚሊዮን ዶላር ብንገነባም ሥራ ባለመጀመራቸው ማሽኖች እየተበላሹ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውንም ሥራ እስኪያጁ ገልጸዋል።
አንድ ባቡር ከሁለት ሜጋ ባይት በላይ ኃይል እንደሚፈልግ የጠቆሙት ኢንጂነር አብዱልከሪም፣ "ፕሮጀክቱ ሲጀመር በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳለ ቃል ከተገባ በኋላ ቆይቶ ሌላ ችግር መፍጠሩ ተገቢ ስላልሆነ መንግስት ማስተካከል አለበት" ብለዋል፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስተሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከማድረጉም ባለፈ በወጪ ንግድ ላይ ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪን እንደሚቆጥብ አመልክተዋል፡፡
"መንግስት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመስራት ይልቅ የተጀመሩት እንዲጠናቀቁ አቋም ወስዶ እየሰራ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በጋራ ተነጋግረን ችግሩን እንፈታለን" ብለዋል፡፡
የዛሬው ጉብኝትና ውይይትም ችግሮችን በትክክል በመለየትና በመረዳት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለግንባታው ካሳ ሳይከፈላቸው የቀሩ 400 አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ያነሱትን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስት መመደቡንና በቅርቡ ክፍያ እንደሚፈጸም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የገጠሙ ችግሮችን በመፍታት ባቡሩ ሥራ እንዲጀምር ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እንደሚሰራ የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ "ባቡሩ በቀን ከ27 ሺህ ቶን በላይ እቃዎችን ወደ ወደብና ማዕከል የሚያጓጉዝ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው" ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ ከፌደራል መንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"የባቡር መስመር ግንባታ ሥራው ሲጀመር የኤሌክትሪክ መስመር እዝርጋታው ጎን ለጎን መካሄድ ነበረበት" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ "ችግሩ በቅርቡ እንዲፈታ እናደርጋለን" ሲሉ አመልክተዋል።
የባቡር መስመሩ የወጪና ገቢ እቃዎች የሚጓጓዙበት በመሆኑ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች አገሮችም ጠቀሜታው የጎል መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ ተመስገን እንዳሉት የባቡር መስመሩ በምስራቅ አማራ የሚመረቱ የፋብሪካ ፣ የግብርና እና ሌሎች ምርቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደጅቡቲ በማጓጓዝ የክልሉን ልማት ያፋጥናል።
የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ሲጠናቀቅ ከአዋሽ ሃራ ገበያ ለመድረስ ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ብቻ እንደሚፈጅ ተመላክቷል፡፡
ባቡሩ በሰዓት ከ120 ኪሎ ሜትር በላይ የሚጓዝ ሲሆን በእዚህም ለንግድና ለሰው እንቅስቃሴ መቀላጠፍ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ይሆናል ተብሏል።