ቀጥታ፡

በዓሉን የምናከብረው ህገ መንግስቱ ያጎናጸፈን መብቶች በመጠበቅ ነው... የመቀሌ ነዋሪዎች

ኢዜአ፤ ህዳር 20/12  በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረውን የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የምናከብረው በህገ መንግስቱ የተጎናጸፍናቸውን መብቶች እንዳይሸራረፉ በመጠበቅ ነው ሲሉ የመቀሌ ከተማ የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

የከተማው ነዋሪና የህግ ምሁር አቶ አፅብሃ ገብረአግዛብሄር በሰጡት አስተያየት በሃገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ለ14ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት የሚከበረውን የብሄር፣ ብሄረሰቦች ና ህዝቦች በዓል በህገ መንግስቱ የተጎናፀፍናቸው መብቶች በመጠበቅ ልናከብረው ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በዓሉ የደረሱብንን ስቃይና መከራዎች እንዲባባሱ በማድረግ ሳይሆን መፍትሄ የሚያገኙበት መንገድ በመሻት መከበር እንዳለበት ገልፀዋል።

በተለይ በሃገሪቱ ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ ልሂቃን ልዩነትን ከመስበክ ይልቅ የህዝቦችን የዘመናት አንድነት፣ይቅር ባይነትና መልካም እሴቶችን በማጠናከር  ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መሁሩ አሳስበዋል ።

ሙሁሩ ለተግባራዊነቱ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ  ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እለቱን የምናከብረው ባህላችንን፣ቋንቋችንና ማንነታችንን ይበልጥ የሚያድግበት መልካም መንገድ በማመቻቸት መሆን ይገባል ያሉት ደግሞ በመቀሌ ከተማ የአድማስ ዩኒቨርስቲ መምህር ግደይ ትኩእ ናቸው።

ዕለቱን ስናከብር በኢትዮጵያ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የቆየውን የአብሮነት እሴት በማጎልበትና በህገ መንግስቱ የተጎናፀፍናቸው መብቶች በመጠበቅ መሆን አለበት ብለዋል።

ይህንኑ እውን እንዲሆን ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውን የቤት ስራ መስራት ይገባናል ያሉት አቶ ግደይ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ወጣቶች በሰላም ሰርተው ማደግ የሚችሉበትን መልካም አጋጣሚ ለመፍጠር ህግና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበር እንደሚገባቸው ምክር ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ሲከበር በህዝቦች መካከል መቃቃር ከሚፈጥሩ ድርጊቶች በመራቅና አንድነትና አብሮነት በማጠናከር መሆን እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ ሌተናል ኮሎኔል ገብረመድህን አረፋይኔ ናቸው።

በየደረጃው የሚገኙ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላትም ታግለው ያረጋገጡትን ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዳይናድ በመጠበቅ ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሌተናል  ኮሎኔል ገብረመድህን አውስተዋል።

በትግራይ ክልል ቀኑን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣በስፖርታዊ ውድድሮች፤በፓናል ውይይቶችና በተሃድሶ መድረኮች ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም