ከአግላይነት ወደ አሳታፊነት

88

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የደርግ ሥርዓትን በመጣል አገሪቷን ከተቆጣጠረ ድፍን 28 አመት ሞላው። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት ዓለም እየተመራ  የኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አርሶ አደሩን የትግል ስትራቴጂያዊ አጋር አድርጌ እታገላለሁ በማለት አራት ብሔራዊ ፓርቲዎችን በማቀፍ ግንባር ፈጥሮ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ፓርቲዎችን ግን እንደ አጋር በመቁጠር በአገራቸው ጉዳይ የበይ ተመልካች በማድረግ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ዘልቋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው ኢህአዴግ፣ ምንም እንኳን በመንግስት አወቃቀር ፌዴራላዊ ስርዓትን ይከተላል ቢባልም በተደጋጋሚ እንደሚነሳው በሕወሓት የበላይነት የሚመራና ለሌሎቹ ብሔራዊ ድርጅቶች እምብዛም ቦታ የሌለው ግንባር ነበር እየተባለ ሲተች እንደነበር ከጥልቅ ታህድሶ ማግስት ሲወራ የነበረ ታሪክ ነው።  በዚህ ሒደት በሁሉም የኢኮኖሚና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ላቅ ያለ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ በፖለቲካ ረገድ ፈቅ ማለት ያልቻለና ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና ለዴሞክራሲ ቦታ የሌለው ሥርዓት ተፈጥሯል በሚል ግንባሩ ክፉኛ ይተቻል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ዮሃንስ ቧያለው እንደገለጹት እና ብዙዎቹም እንደሚስማሙበት በአለም ደረጃ በመሪነት ያሉ ፓርቲዎች ለብዙ ዘመናት ግንባር ፈጥረው የቆዩበት ታሪክ የእኛው ኢህአዴግ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። በመሰረቱ ፓርቲዎች በግንባር የሚደራጁበት ዋነኛው እና መሰረታዊ ምክንያት በስልጣን ላይ ያለን መንግስት ተባብረው ለመጣል የሚፈጥሩት ስትራቴጂካዊ አካሄድ እንደሆነ ገልጸው፤ አሸንፈውም ወደ ስልጣን ከመጡም በኋላ እራሳቸውን ችለውና አገራዊ ፓርቲ እስኪመሰርቱ ድረስ የተወሰነ ምርጫ ለማሸነፍ ሲባል ድምር ድምጽን ለማግኘት ያውና ያው ባይሆኑም ተቀራራቢ ፍላጎታቸውን በማሰባሰብ እንደሚጠቀሙበት አቶ ዮሃንስ አብራርተዋል። በመቀጠልም በግምባር ደረጃ ኢህአዴግ በአለም ላይ ብቸኛው አገራዊ ፓርቲም እንደሆነ ያስረዳሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በግንባርነት የቆየው ኢህአዴግ የአንድ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ራዕይ ማሳካት አለመቻሉን የገለጹት ደግሞ በኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ  ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ናቸው። ይህም የሆነው ይላሉ ሀላፊው፤ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የተወሰነ የሉዓላዊ ባህሪ በመፍጠር በተቀናጀ አስተሳስብ አገር ለመምራት የሚያስችል አቋም ላይ ባለመድረሳቸው መሆኑን አብራርተው፤ በሌሎች ተመሳሳይ በፌዴራሊዝም ስርዓት የሚተዳደሩ አገሮች ያለው ተሞክሮ ይህንን ያሳያል ሲሉም አስረድተዋል። ከእነዚህ አገራት መካከል ለአብነትም በህንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ቤልጅየምና ናይጄሪያ የሚገኙ ፓርቲዎች አገር አቀፍ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። ኢህአዴግም በጥናት ላይ የተመሰረተ ከግንባርነት ወደ አገራዊ ውህድ ፓርቲ  በመቀየሩ የግንባሩ አባላትና አጋር ድርጅቶች በውህደቱ ምክንያት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጥላ ስር ለመሰባሰብ የሚያስችል ዣንጥላ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢህኣዴግ በተለያዩ የምክር ቤት ጉባኤዎች በተደጋጋሚ  እንደሚነሳው  በግንባሩ አባል ፓርቲዎች መካከል የውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ልዩነት ባይኖርም፣ ከውህደት አስቀድሞ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችና ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በተመሳሳይ ገጽ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው ረዥም ጊዜ የወሰዱ ክርክሮች በአባል ፓርቲዎች መካከል ሲደረጉ እንደቆዩ በተደጋጋሚ ሲሰማ ቆይቷል።

ለዚህ ደግሞ ማሳያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ግንባሩን ወደ አንድ ውህድ አገራዊ ፓርቲ ማሸጋገር ምክንያታዊ ነው ብለው ያምኑ እንደነበር የኢትዮጵያ ብሮድካስቲግ ኮርፖሬሽን የሰራቸው ፕሮግራሞች  ያሳያሉ። በመሆኑም በብሔር ማንነት ላይ በማተኮርና አገራዊ ማንነትን በመዘንጋት ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲደበዝዝ አድርጌያለሁ በማለት ራሱን የገመገመው ኢሕአዴግ፣ ግንባሩን ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ማምጣት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል። እናም ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ አገራዊ ውህድ ፓርቲ ለመምጣት እና ዘመኑን የሚመጥን ፓርቲ ለማድረግ የሰባት ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ በማሳለፍ ውህደቱን ዕውን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የጥናቱ አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ስነ ባህሪ ጥናት ኮሌጅ መምህር  ዶክተር ሙሉ ነጋ ተናግረዋል።

እንደ ዶክተሩ ገለጻ ከሆነ በተለይ የኢህአዴግን ውህደት በተመለከተ የ28 ሀገራት ተሞክሮ እንደታየና ከዚህ ውስጥ ደግሞ የቤልጂየም፣ ስዊዘርላንድ፤ ናይጀሪያን ከመሳሰሉ ሰባት ሀገራት የፌዴራሊዝም የፓርቲ አሰራር ላይ ጥናት ተደርጎ ልምዶች መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ሙያዊ አሰራሩን ተከትሎ በገለልተኛ ባለሙያዎች የተጠናውን የውህደት ጥናት ኢህአዴግ ወስዶ ለውይይት አቅርቦታል። በዚህም መሰረት ሀገራዊ አስተሳሰብ ያለው እና ሁሉንም ዜጎች ያሳተፈ አካሄድ ያላቸው የአውሮፓ፤ አሜሪካ እና አፍሪካ አገራት ተሞክሮ ተግባራዊ እንደተደረገም ተናግረዋል። በጥናቱ የተካተቱ ሀገራት የፖለቲካ አካሄድ ልዩነት ቢኖረውም አብዛኞቹ በሀገራዊ ጥንካሬ ላይ ተመስርተው እንደሚሰሩ መታየቱን የጠቆሙት ዶክተር ሙሉ፣ ለአብነት በቤልጂየም ሶስት ፓርቲዎች በጥምር መንግስት በመመስረት ስለቤልጂየም ሀገራዊ ጥንካሬ አላማ አድርገው እንደሚሰሩ እና ተሳትፎአቸውም በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮዽያ ፌዴራሊዝም ስርዓት እንደሚያሳየው ራስን በራስ የማስተዳደር ስርዓት በስልጣን ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ሲሆን በሕገመንግስቱ ምዕራፍ 4 አንቀጽ 45 ላይ ‹‹ኢትዮጵያ የፓርላሜንታዊ ስርዓት›› ተከታይ ስለመሆኗ በግልጽ ተመላክቷል። የፌዴራሊዝም ስርዓትን አስፈላጊ (ተመራጭ) ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ብዝሃነትን ማስተናገድ ማስቻሉ፣ በርካታ ማንነቶች ባላት ሀገር ውስጥ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን የሚመልስ መሆኑ፤ ሀገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል ተመራጭ መሆኑ ይጠቀሳል ያሉት ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ እንዳልካቸው ምንዳ ናቸው፡፡ በብዝሃነት ለተዋበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፌዴራሊዝም የአስተዳደር ስርዓት የተሻለ አማራጭ አይኖርም ባይ ናቸው፡፡

ይህም አካታችነት፣ ማህበራዊ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ላይ የበለጠ እንዲሰሩ ውህደቱ ያግዛቸዋል መባሉን በማስረዳት ይገልጻሉ። በመሆኑም ይላሉ የህግ ባለሙያው አገሪቷ ግን እስከ አሁን በነበረው አካሄድ አራት ብሔራዊ ድርጅቶችን ብቻ ወሳኝ ቦታ ላይ በማስቀመጥ አጋር የተባሉ ፓርቲዎችን አግልሎ የቆየ ሲሆን አሁን ኢህአዴግ ወደ ውህደት በማምራቱ ችግሩን ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የውህድ ፓርቲው ጥቅሞች

የግንባሩን ወደ አንድ ውህድ የመምጣት አስፈላጊነት ለዓመታት ሲንከባለል ከመቆየቱም በላይ ሂደቱ መቼ፣ እንዴትና በማን ይከወን የሚለውም ቁርጥ ሆኖ አልተነገረም ነበር፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግ ወደ አንድ ፓርቲ ቢያድግ ሊያስገኛቸው የሚችላቸውን ድርጅታዊና አገራዊ ጥቅሞችን በመተንተን ውህደቱ የሚከወንበትን ሒደት በሚመለከት ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይኼ ጥናት በተለይ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ በተደረገው የፓርቲው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ተነስቶ ጥናቱን የግንባሩ ምክር ቤት እንዲመራውና በቀጣዩ የግንባሩ ጉባዔ ላይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት እንዲወሰን ከስምምነት ተደርሶ እንደነበረ ከኢህአዴግ ም/ቤት የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

በመሆኑም ይህ አሁን አገር አቀፍ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ አጋር ፓርቲዎችን አባል ከማረጉም በላይ አራቱንም ብሄራዊ ፓርቲዎች ወደ መሃል በማሰባሰብ አካታችነቱ የጎላ እንደሆነ መተዳደሪያ ደምቡ ያስረዳል። ከአካታችነቱም በተጨማሪም ፓርቲዎች መዋህዳቸው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት አንድነትን ከማጠናከር አንጻርም የራሱ ድርሻ እንዳለው ነው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል ዶ/ር አለሙ ስሜ የተናገሩት።

እንደ ዶክተር አለሙ ገለጻ ከዚህ በፊት በጥምረት በቆየባቸው ጊዜያት የፍትሐዊ ውክልና እጥረት እንዳለበት ጠቁመው አሁን ውህደቱ የውስጠ ዴሞክራሲያዊ አሰራሩን በማዳበር ፍትአዊ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ሲሉ ተናግረዋል። ሌላው ከፖለቲካዊ አደረጃጀት ጥቅም አንጻርም የጎላ ድርሻ ያለው ነው ሲሉም አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ሚዛኑን የጠበቀ አገራዊ አንድነትን በመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊና ክልሎች የአገሪቷ መሪ ለመሆን ዕድልን መንፈጉ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ዜጎች እኩል የመሳተፍና የመወሰን መብት እንዳይኖራቸው አድርጎ የቆየውን አሰራር ይቀርፋል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ደግሞ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው። ኢህአዴግ የራሱን አካሄድ አይቶና ገምግሞ አሰራሩን ለማስተካከል ስምምነት ላይ መድረሱ የአገሪቱን ዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ሲሉም ተናግረዋል። በተጨማሪም አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንደገለጹት፤ “ማህበራዊ መሰረታችሁ አርሶ አደር አይደለም” የሚለው ሃሳብ አጋር ድርጅቶች ወደ ግንባሩ እንዳይቀላቀሉ ያደረገ ዋነኛ ምክንያት ነው። ነገር ግን የግንባሩ እህት ድርጅቶች በሚመሯቸው ክልሎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ቁጥር አጋር ድርጅቶች ከሚመሯቸው ክልሎች እንደሚበልጥም ነው ያመለከቱት።

ድርጅቱ በጥምረት ሲሰራ በቆየበት ወቅት አሰራሩ አጋር ድርጅቶቹ ባልተሳተፉበት ሁኔታ በእጅ አዙር የኢህአዴግን ውሳኔ እንዲያስፈጽሙ ሲደረግ መቆየቱን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል። በመሆኑም ውህደቱ የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነትንና የሞግዚት አስተዳዳርን በማስቀረት ክልሎች ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ስርዓትን  እንዲተገብሩ ያስችላል ነው ያሉት። ኢህአዴግ ወደ ውህደት ሲመጣ ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋዎችን እንደሚጠቀም  ገልጸው፤ ይህም ብዝሃ ልሳን ያላቸውን ዜጎች በመፍጠር ለአገራዊ አንድነት ፋይዳው የጎላ  መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል  የሚካሄደው ውህደት በጥናት ላይ ተመስርቶ  የብሔረሰቦችን ብዝሃነት፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና ሌሎችም ጉዳዮች አጽንኦት የሰጠ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የቤንሻንጉል ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሀላፊው መለሰ በየነ ናቸው። ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ፌደራሊዝም በሚገባ ተግባራዊ እንዳልሆነ ያስታወሱት  አቶ መለሰ ውሕዱ ፓርቲ እውነተኛ ፌደራሊዝም በመተግበር ህዝብን ያሳተፈ የላቀ ሥራ እንደሚጠብቀው አስታውቀዋል፡፡

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጸጋዬ ብርሃኑ እንዳሉት ኢህአዴግ ለመዋሃድ መወሰኑ የሚበረታታና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ተደቅኖ የነበረውን የህልውና ስጋትን ያቃለለ ነው። አክለውም ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያመላክት እንደሆነ ጠቁመው፤ በሃገሪቱ የሃሳብ የበላይነት እንዲያድግ በር እንደሚከፍትም ጠቅሰዋል። “የድርጅቱን ውህደት አሃዳዊ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ነው” በሚል በአንዳንድ አካላት በሚነሳው አስተያየት እንደማይስማሙም ተናግረዋል።ይህ አይነት አመለካከት ጥቂት ግለሰቦች የግል ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበትን ስልጣን ለማስቀጠል በመፈለግ ለውህደቱ የተለያየ ስያሜ ለመስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።

ግንባሩ በአሁኑ ወቅት በውሳኔ ሰጭነት የማይሳተፉ አምስት አጋር ድርጅቶችን አካቶ ይዟል። በመሆኑም ውህደቱ ፈዴራላዊ ሥርዓቱን በማጎልበት አገራዊ አንድነት ለመፍጠር ዕድል የሚሰጥ ነው ያሉት ምሁራኑ፤ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት አገር ያስተዳደረው ”ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሳይሆን የክልሎች ግንባር ሆኖ ነው” ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል።

አሁን ካለው የሕዝብ ጥያቄ አንጻር ኢህአዴግ እንደ ግንባር ሆኖ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ አጋር የተባሉትን ፓርቲዎችን በማካተት የተዋሃደ ፓርቲ መሆን ያስፈልገዋል ብለው እንደሚያምኑም  ነው ምሁራኑ የተናገሩት።  እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን አንዳንድ ሰዎችም ሆነ ፓርቲዎች ውህደቱን ሲያጣጥሉ እና ሲቃወሙ ይደመጣል። እነዚህ አካላት እንደ መከራከሪያ ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል የመጀመሪያው የቅደም ተከተል ጥያቄ የመጀመሪያው ነው። በዚህም በግንባሩ አባል ፓርቲዎች መካከል የውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ልዩነት ባይኖርም፣ ከውህደት አስቀድሞ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችና ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በተመሳሳይ ገጽ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው ህወሃት እንደ ፓርቲ ውህደቱን አልቀበልም ሲል ይደመጣል። እንደ ፓርቲው ገለጻ ከሆነ ኢህአዴግን ማዋሃድና አንድ አገራዊ ፓርቲ የሚፈጥር አሰራርና አደረጃጀት ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ለመመስረት የሚደረግ ሂደት ነው ሲሉም ይከሳሉ። ነገር ግን ይህን በተመለከተ በጥናቱ እንደተገለጸውና የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና አጋር ፓርቲዎች እንደሚስማሙበት በግንባር ላይ የሚገኘውን ድርጅት ወደ አገራዊ እና ዘመኑን የሚመጥን ወጥ የሆነ ፓርቲ ለመፍጠር እንደሆነ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አገር አቀፍ ፓርቲ ምን መልክና ርዕዮተ ዓለማዊ ወገንተኝነት እንደሚኖረው ያልተነገረ ሲሆን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ግን ሊከተል እንደማይቻል በግንባሩ አባል ድርጅቶች እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ማሳያ ናቸው ሲሉም ይሞግታሉ። ለነገሩ ኢህአዴግ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ ሲመጣ የርዕዮትም የሆነ የመተዳደሪያ ደምብ ሊቀይር እንደሚችል በጊዜው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን በ5ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ መድረክ ላይ ጠቁመው እንደነበር የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።   ሕወሓት ግን ግንባሩን በፍጥነት ወደ ውህደት መምራት ኢሕአዴግን ወደ ሞት የሚሸኘው እንደሆነ በማስጠንቀቅ፣ ይህ የሚሆን ከሆነ ግን ከሌሎች ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ግንባር እንደሚፈጥር ገልጾ የውህድ ፓርቲው አካል እንደማይሆን በተደጋጋሚ  ስገለጽ ይደመጣል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞችና ሕወሓት ከአሁን ቀደም በግንባሩ ውስጥ የነበረውን የበላይነት በማጣቱና ፓርቲው የሚዋሃድ ከሆነም ይህ የበላይነት ይበልጡኑ በመጥፋት በግንባሩ የነበረው የባለቤትነት አስተሳሰብ ይከስማል ይላሉ፡፡ ለዚህ ነው ከህወሃት በስተቀር ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን ጨምሮ እህት ድርጅቶች ውህደቱን በፍጥነት በመቀበል እና በምክር ቤታቸው በማስወሰን ለመቀላቀል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት በማለትም ያስረዳሉ።

ይህ አገራዊ ፓርቲ ሲፈጠር አባል ድርጅቶች ውህደቱን የሚፈጥሩት በፕሮግራም ተመሳሳይነት ያላቸውና በዓላማው ያመኑ ስለሚሆኑ በአንድ መንፈስ ህዝቦችን አስተባብረው በመስራት ወደታሰበው አገራዊ ብልጽግና ሊያደርሱ እንደሚችሉ የብዙዎች እምነት ነው። ስለሆነም ወዲህ እና ወዲያ ከመጓተት የሀገሪቱን ህዝብ በአንድ አገራዊ ዣንጥላ ስር የሚያሰባስበንን አመራጭ በመከተል  ለተግበራዊነቱ እንስራ መልዕክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም