ዩኒቨርሲቲው የማሽላ ምርታማነትን ለማሻሻል የ20 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የማሽላ ምርታማነትን ለማሻሻል የ20 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት እያካሄደ ነው
ኢዜአ ህዳር 19 / 2012 ዓም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የማሽላ ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችል የ20 ሚሊዮን ብር የምርምርና የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በፕሮጀክቱ የመጀመርያ ምዕራፍ አፈጻጸም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመከረበት የሁለት ቀን የውይይት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል። ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌ ከተማ በወቅቱ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ድርቅን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የማሽላ ዝርያ በማፍለቅ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ ነው። በዩኒቨርሲቲው የግብርና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ፍቃዱ ምትኩ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ እየተካሄደ ያለው ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትና ከቢልና ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል። ከአሜሪካው ጆርጂያ ዩኒቨርሲቲና ከአውስትራሊያው ዩስላንድ ዩኒቨርሲቲ በኩልም ለፕሮጀክቱ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገለጸዋል ። በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስድስት ዓመት ውስጥ ለምርምር የሚያገለግሉ የሞለኪውላር ቤተ -ሙከራ ግንባታ፣ የመሳሪያዎች ተከላና ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። በዘርፉ ለ11 ባለሙያዎች በሦስተኛና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም ከ70 በላይ አጫጭር ስልጠናዎች መሰጠታቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል። ዶክተር ፍቃዱ እንዳሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማሽላ ልማት ተስማሚ ስነ ምህዳር ያላቸው አካባቢዎች ተለይተዋል። “በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራት ከዚህ በፊት በምርምር ወጥተው አርሶአደሩ እየተጠቀመባቸው የሚገኙ ምርጥ ዘሮችን ለማስቀጠልና አዲስ ዘር ለማፍለቅ የሚያግዙ ናቸው” ያሉት ደግሞ የዘርፉ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን ባንቴ ናቸው ። በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰበል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ታደሰ ዩኒቨርሲቲው ድርቅ በማሽላ ሰብል ላይ እያስከተለ ያለውን የምርት መቀነስ ችግር ለመፍታት የጀመረው ስራ የመንግስትን የልማት አቀጣጫ የሚደግፍ መሆኑን አመላክተዋል ። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ተቋሙ በምርምር መሰረተ ልማትና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ያከናወናቸው ተግባራት ድርቅን የሚቋቋሙ የማሽላ ዝርያዎችን በማፍለቅ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ጠቀሜታ አላቸው። በአገሪቱ አሁን ባለው ሁኔታ በሄክታር እየተገኘ ያለው አማካኝ የማሽላ ምርት 27 ኩንታል መሆኑን ተናግረዋል። ልማቱ በተገቢው ምርምርና ቴክኖሎጂ ከታገዘ በሄክታር የሚገኘውን አማካኝ የሰብሉን ምርት እስከ 120 ኩንታል ለማሳደግ እንደሚቻል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።በውይይት መደረኩ የምርምር ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።