በጌዴኦ ዞን በሂሳብ ምርመራ የተለየን የገንዘብ ግኝት የማስመለስ ጥረቱ ደካማ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ዞን በሂሳብ ምርመራ የተለየን የገንዘብ ግኝት የማስመለስ ጥረቱ ደካማ መሆኑ ተገለጸ
ኢዜአ ህዳር 19/2012 በጌዴኦ ዞን በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሂሳብ ምርመራ ግኝት ቢለይም ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑ ተገለጸ። በሂሳብ ምርመራ ግኝት ዙሪያ በተደረገ የምክክር መድረክ የኦዲት ግብረ ኃይል እንዳለው የመንግስት ሀብትና ንብረት በተለያዩ ምክንያቶች ሲባክን በሂሳብ ምርመራ ቢደረስበትም ከማስመለስ አንጻር ክፍተት አለ። ከግብረ ኃይሉ አባላት መካከል የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ የምርመራው ግኝት ከአስር ዓመት በላይ ሳይሰበሰብ ከቆየ ህጉ በይርጋ እንዲቆም ስለሚያደርግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሂሳብ ምርመራ ግኝት የችሎት ክርክሮች በመረጃ አለመደገፍና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አለመሆን የማስመለስ ሂደቱን ፈተና ላይ መጣላቸውን ጠቁመዋል። በግኝቱ መሰረት የሚወሰደው እርምጃ ደካማ መሆን የባድርሻ አካላት ተቀናጅቶ የመስራት ክፍተትም ይስተዋላል። “የኦዲት ግኝት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መረጃ በማጥራቱ ረገድ ባድርሻ አካላት በቅንጅት መሰራት አለባቸው “ብለዋል። በግለሰቦች እና በተቋማት ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር ተጠያቂዎችን ለይቶ ለህግ እንዲቀርቡ የማድረጉ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል። የዞኑ ፋይናንስ ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከባዱ ወራሳ በበኩላቸው በዞኑ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት በሂሳብ ምርመራ ግኝት ቢለይም የማስመለስ ሂደት ደካማ መሆኑን ተናግረዋል መሆን ተናግረዋል። ይህም የፋይናንስ ሂደቱ ላይ ጫና አሳድሯል። በተካሄደው የሂስብ ምርመራ ከግብዓት ጋር በተያያዘ ከ66 ሚሊዮን 600ሺህ ብር በላይ ግኝት መኖሩን ገልጸዋል። በተጨማሪም ያልተወራረደ የውሎ አበልና ተገቢ ባልሆነ መልኩ የተከፈለ 7 ሚሊዮን 500ሺህ ብር መገኘቱም ጠቁመዋል። በዞኑ ምክር ቤት የፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር በሽር በበኩላቸው ተመሳሳይ የሀብት ብክነት እንደይከሰት የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።በተለያዩ ምክንያቶች ባክኖ ለምክር ቤቱ የሚቀርበው የሀብት መጠን ስርዓት ያለማሲያዝ በልማት ስራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አመልክተዋል። “የመንግስት ሀብትና ንብረት ለልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍቻ መዋል ሲገባው የግለሰቦች ሃብት ማካበቻ መሆኑ ተገቢ አይደለም “ ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ የምስራች ገመዴ ናቸው። ግኝት ያለባቸውን ግለሰቦቹ በህግ ተጠያቂ ማድረግና የመንግስት ሀብትን በአግባቡ በመሰብሰብ ለተገቢው ልማት እንዲውል ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በዲላ ከተማ ትናንት በተካሄደው የምክክር መድረኩ የወረዳ እና ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤዎች፣ ቋሚ ኮሚቴዎች፣ አስተዳዳሪዎች፣ የፍትህ አካላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።