ቀጥታ፡

14ኛው የብሔር ብሄረሰቦች በዓል በጋምቤላ መከበር ተጀመረ

ኢዜአ፤ ህዳር 19 / 2012 ዓ.ም  ህገ መንግስትና አገራዊ ለውጡ የፈጠራቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምና ልማትን በክልሉ ለማረጋገጥ ሁሉም ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ ።

``ህገመንግስታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም ” በሚል መሪ ቃል 14ኛው የኢትዮጰያ ብሔር ብሐረሰቦች ክብረ በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ በፓናል ውይይት ዛሬ መከበር ጀምሯል።

አፈ ጉባኤው አቶ ላክደር  ላክባክ  በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ህገመንግስቱና ሀገራዊ ለውጡ የፈጠራቸው አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትጋት መስራት ይገባል።

ህገመንግስቱ ፀድቆ የፌዴራሊዝም ስርዓት ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ማግስት ጀምሮ የክልሉ ህዝብ እንደማንኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የእኩልነት መብት ተረጋግጦ እራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር በርካታ ስኬቶች ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ በነበረው የአተገባበር ችግር የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ ያልሆነባቸውና የተገለለባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩም አንስተዋል ።

በተለይም ጋምቤላን ጨምሮ አጋር ተብለው የሚጠሩ አምስቱ የክልል ህዝቦች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል የመወሰን መብት ተነፍጓቸው መቆየቱ የፌዴራሊዝም  ስርዓቱ የአተገባበር  ችግር ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን ላይ እንደ ሀገር በተጀመረው ለውጥ  እውነተኛ ፌዴራሊዝም  ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል የሚወስኑበትና ተሳታፊ የሚሆኑበት የለውጥ ምእራፍ መፈጠሩን ገልፀዋል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው በቅርቡ የተደረገው የኢህዴግና አጋር ድርጅቶች ውህደት ነው ብለዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የክልሉ ህዝቦች ተነፍገውት የነበረውን በሃገራቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን መብት በተጎናፀፉበት የለውጥ ምእራፍ ላይ ሆኖ ስለሚከበረው የተለየ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የክልሉ ርእስ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በሃገሪቱ እየተተገበረ ያለው ስርዓት እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባለበት አገር አማራጭ የሌለው ስርዓት መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ አተገባበር ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል ።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ሳይሸራረፍ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ከተደረገ የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለት በክልል ደረጃ በፓናል ውይይት የተጀመረው የብሔር ብሐረረሰቦች በዓል በነገው እለት በሰልፍ ትርኢት ፣ በባህላዊ ጭፈራዎችና በሌሎችም ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሮ እንደሚውል ለበዓሉ ከወጣው የድርጊት መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም