ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ኢዜአ፤ ህዳር 19/2012 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልገሎት ክልል አቀፍ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ትናንት አካሄዷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መስሪያ ቤቱ በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በኃይል መቆራረጥ፣ በወራዊ ክፍያና በሌሎችም ዘርፎች ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ካን ጋልዋክ እንዳሉት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም የኃይል መቆራረጥና ለቆጣሪ ፈላጊ ደንበኞችን ፈጣን መስተንግዶ በመስጠት በኩል ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በዚህ ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በተለይም በዞኖችና በወረዳዎች የኃይል አቅርቦት ከአንድ ሳምንት በላይ እየተቋረጠ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽህኖ እያሳደረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ኡጁሉ ኡሎክ ናቸው።

አቶ ኡሞድ ኡቻላ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው በቅርቡ ተሻሽሎ የመጣው ወራሀዊ የክፍያ ታሪፍ የተጋነነና ግልጽነት የጎደለው ከመሆኑም በላይ ቅሬታዎችን ያለማስተናገድ ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

“ቅንጅታዊ አሰራር ባለመኖሩም በተለይ በጋምቤላ ከተማ የኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎች ከመሪ ፕላን ውጪ እየተተከሉ በመንገድ ከፈታ ወቅት ለማስነሻ ተገቢ ያለሆኑ ክፍያዎች እየተፈፀሙ ይገኛሉ” ብለዋል።

በመሆኑም መስሪያቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ሊያጠናክር እንደሚገባ አቶ ኡጁሉ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጋምቤላ ክልል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቢቂላ ዋቅጅራ በተነሱን ሃሳቦች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ውዝፍ ያለባቸው ደንበኞች ካልሆኑ በስተቀር ብዙ የተለየ ክፍያ አለመጠየቁን ነው የገለጹት።

ቀደም ሲል በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ምንም መሪ ፕላን ሳይኖር የተተከሉ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ከመንገድ ከፈታ ጋር ተያይዞ ሲነሱ የሃብት ብክነት እየተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በአገልገሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ከመፍጠሩ ባለፈ ለተቋሙ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በዞኖችና በወረዳዎች የኃይል መቆራረጥ ችግር አለ ተብሎ የተነሳውን ሃሳብ ያመኑት አቶ ቢቂላ፣ ችግሩን ለማቃለል በዕቅድ ተካቶ እየተሰራ መሆኑን አመልከተዋል።

በተጨማሪም የመብራት ቆጣሪ ፈላጊ ደንበኞችን በዘንደሮው ዓመት በተሻለ ፍጥነት ለማስተናገድ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፣ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ከ12 ሺህ በላይ አዲስ ደንበኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው “ከቅንጅታዊ አስራርና ከደንበኞች አገልግሎት ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን ለመፍታት መስሪያ ቤቱ በትኩረት ይሰራል “ብለዋል።

የምክክር መድረኩም ክፍተቶችን በመለየት ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም አቶ ሽፈራው ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መስሪያ ቤቱ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የኃይል አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ ለሚከናወናቸው ስራዎች ስኬታማነት የክልሉ መንግስት የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል።

በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለልማት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ ለሚከናወኑ ሥራዎች መቃናት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው በእዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ባከለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም