የምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ጋር ሲያካሂድ የነበረው ውይይት ባለመግባባት ተበተነ - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ጋር ሲያካሂድ የነበረው ውይይት ባለመግባባት ተበተነ
ኢዜአ ህዳር 19/2012 በፓርቲዎች ምዝገባ ማስፈሚያ አዋጅ ላይ በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት የጠራው ስብሰባ ባለመግባባት ተበተነ። ቦርዱ የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣይ ጥያቄያቸውን አቅርበው ውይይቱ እንደሚደረግ ቃል ገብቶ ሸኝቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ በነጋሪት ጋዜጣ በወጣው አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን ለማስፈጸም የአዋጅ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ለማወያየት በዛሬው ዕለት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ከረፋዱ ሶስት ሰዓት በተጀመረው የውይይት መድረክ ሲንጸባረቅ የነበረው ግን ከዕለታዊ አጀንዳው ይልቅ 'የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህልውና የሚገዳደር ነው' በሚል የተቃወምነው የምርጫና የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መጽደቅ አልነበረበትም፤ ያቀረብነው ጥያቄም ምላሽ አላገኘም' በሚል ሃሳብ ላይ ያጠነጠነ ነበር። በዚህም የምርጫ ቦርዱን ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን ጨምሮ የቦርድ አባላትና በረቂቅ ደንቡ ዝግጅት ተሳታፊዎች ተወያዮቹ ወደ ዕለታዊ አጀንዳ እንዲመለሱ ቢጠይቁም ተወያዮቹ ግን አልተስማሙም። ሰብሳቢዋ ምርጫ ቦርድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው አዋጅ ላይ ከዚህ በኋላ ስልጣን እንደሌለውና በአዋጁ ላይ መወያየትም ውጤት እንደማያመጣ አስረድተዋል። ከዛ ይልቅ አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ እንደ ባለድርሻ አካላት ሃሳብ እንዲሰጡ፤ አዋጁ ይሻሻል ቢባልም እንኳን በምክር ቤቱ የራሱ አሰራር እንዳለው በመጠቆም፣ ፓርቲዎቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ወደፊት ሌላ መድረክ አጀንዳ ፈጥሮ ማወያየት እንደሚቻል ቢያግባቡም ተሳታፊዎቹ አልተስማሙም። የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ግን "ከዚህ በፊት በአዋጁ ረቂቅ ላይ የሰጠነው ሃሳብ ግብዓት ሆኖ ባለማገልገሉ አሁን በዚህ ደንብ ላይ የምንሰጠው አስተያየት ግብዓት ይሆናል የሚል እምነት የለንም" ብለዋል። "በመሆኑም የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ለማስፈጸም በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ከመወያየታችን በፊት በአዋጁ ላይ ያነሳነው ጥያቄ ሊመለስልን ይገባል" ሲሉ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል። በዚህ የተነሳም ለግማሽ ቀን ተጠርቶ የነበረው መድረክ ካለስምምነት የተበተነ ሲሆን ተወያዮቹም የምሳ ግብዣ ተደርጎላቸው ተሸኝተዋል። የቦርዱ ሰብሳቢም በቀጣይ ፓርቲዎች ጥያቄዎቻቸውን በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ሆነ በተናጠል በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ጠይቀው፤ ረቂቅ ሰነዱን እንደቀላል ነገር ሳይመለከቱ እንዲወያዩበት ጠይቀዋል። በመድረኩ መቀጠል ባለመቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሌላ ጊዜ ለውይይት ተዘጋጅተው እንዲመጡ በማሳሰብ፣ አሰናብተዋል። ስብሰባው ከተበተነ በኋላ የቦርድ ሰብሳቢዋ በሰጡት መግለጫ ቦርዱ የማስፈጸም ግዴታ ስላለበት ረቂቅ ደንቡ ላይ ፓርቲዎቹ ተወያዩበትም፤ አልተወያዩበትም መጽደቁ እንደማይቀር አረጋግጠዋል። ውይይቱ ደንቡ የፓርቲዎች እንቅስቃሴ የሚገዛ በመሆኑ ወደፊት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር ተወያይቶ በጋራ ለመቅረፍና መርሆች እንዲፈጸም ያስችላል ነው ያሉት። ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ማቅረብ ቢችሉም በጸደቀው አዋጁ ላይ አንቀጾችን እየጠቀሱ መከራከር ፋይዳ ቢስ መሆኑን ጠቅሰዋል። አገራዊ ምርጫን ማደረጃትና ማስፈጸም ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሪት ብርቱካን፤ ትክክለኛና ተዓማኒ ምርጫ ለማድረግ ከፓርቲ ጉዳዮች በተጨማሪ ሲቪክ ማኅበራትና ሚዲያዎችን በተመለከተ ግብዓት እንደሚሰበስብ ገልጸዋል። ፓርቲዎች ሃሳባቸውን መግለጽ መብታቸው ቢሆንም "በማይለወጡ ጉዳዮች ላይ ስንከራከር አንከርምም፤ ቦርዱ ደንብና መመሪያውን ማውጣትና ለምርጫው የማደረጃት ኃላፊነቱን ይወጣል" ብለዋል።