ቀጥታ፡

ውህደቱ ለአርብቶ አደሩ መልካም እድሎችን ይዞ የመጣ ነው ... በአፋር ምሁራንና የፖርቲ አመራሮች

ሰመራ (ኢዜአ) ህዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም-  የኢህአዴግ ውህደት ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ መልካም እድሎችን ይዞ የመጣ ነው ሲሉ በአፋር ክልል የሚገኙ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ። የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሲቪክና ስነ-ዜጋ መምህር አቶ ሙክታር ጠይብ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አርብቶ አደሩ ለአብዮዊታዊ ዴሞክራሲ የሚሆን ማህበራዊ መሰረት የለውም በሚል በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ እኩል የመወሰንና የመሳተፍ እድል ተነፍጎት ቆይቷል ። በአገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ የአርብቶ አደሩን ውክልናና እውቅና የነፈገ እንደነበር አስታውሰዋል። በዓመታቱ የነበሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም የማህበረሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡና ኑሮውንም ያላሻሻሉ እንደነበሩ ጠቁመዋል። በኢህአዴግ አባላትና አጋር ድርጅቶች የተደረገው ውህደት አርብቶ አደሩን በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመሳተፍ እንዲሁም ፍላጎቶቹንና ጥቅሞቹን የሚያስከብርለት መሆኑን ተናግረዋል። ሌላው በዩኒቨርሲቲው የሲቪክና ስነ-ዜጋ መምህር አቶ እስጢፋኖስ ባለው በበኩላቸው "የኢህአዴግ የፖለቲካ አደረጃጀት አጋር ድርጅት በሚል አርብቶ አደሩን አግልሎ ቆይቷል" ብለዋል ። የፖለቲካ አደረጃጀቱ በክልሎች መካከል እኩልነትን በመንፈግ አንዱን ሰጪ ሌላውን ተቀባይ አድርጎ በመሳል የተረጂነት ስሜትን ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል ። "ውህደቱ ለአርብቶ አደሩ በህገ-መንግስቱ የተሰጡ ፍትሃዊ ውክልናን ያረጋግጣል" ሲሉም ገልጸዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች አገርንና ህዝብን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሻግር የሚችል የሃሳብ ልዕልና ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ መሆኑንም አመላክተዋል። እንደአቶ እሰጢፋኖስ ገለጻ ውህደቱ የአርብቶ አደሩ ልጆች ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበት እድል ይፈጥራል። “ውህደቱ አርብቶ አደሩ በአገራዊ ጉዳይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆን እድል የሰጠ ነው” ያሉት ደግሞ የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀንፈሬ መሐመድ ናቸው። “ውህደቱ ለአፋር ህዝብ የዘመናት ህገ-መንግሰታዊ ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው” ሲሉም ተናግረዋል ። በውህደቱ አፋርኛ የፓርቲው የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ከተወሰኑ ሌሎች ቋንቋዎች አንዱ መደረጉም አርብቶ አደሩ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ያለውን ቀረቤታና መስተጋብር የሚያጠናክር መሆኑን አመላክተዋል ። የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (አርዱፍ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሐመድ አወል በበኩላቸው “ውህድ ፓርቲው በአገራችን እየጎላ የመጣውን አክራሪ ብሔርተኝነት በማርገብ አገራዊ ማንነቶች እንዲጎለብቱ ያደርጋል” ብለዋል። እስከዛሬ የአፋር ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ ባሉ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ፍትሃዊ ተሳትፎ ያልነበረው መሆኑ  በልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የአርብቶ አደሩ የልማት ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ እንዳይመለስ አድርጎ መቆየቱን ተናግረዋል። እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ ውህደቱ እነዚህንና መሰል ክፍተቶችን በመሙላት አርብቶ አደሩ ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲኖረው እድል የሚፈጥር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም