ቀጥታ፡

የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማበረታታት በኤሌክትሪክ ሃይል ዘርፍ ያለውን ኢንቨስትመንት ማበረታታት አለብን

ህዳር 19/2012 የሃገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማበረታታት ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሃይል ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት አድርጋ እንደምትሰራ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና ተናገሩ። የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (GIZ) ሶስተኛውን ዙር የኢትዮጵያ የኃይል ልማት /EnDev Ethiopia/ ፕሮግራም ትናንት ይፋ አድርጓል። ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም ሲሆን ይህ የሶስተኛው ዙር ፕሮግራም ደግሞ ስደተኛ ካምፕ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው። በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና "በኢትዮጵያ ላለው ስራ ፈላጊ ወጣት ስራ ለመፍጠርና የሃገሪቷን ዘርፈ ብዙ እድገቶች ለማስቀጠል የኃይል ዘርፉ ላይ ትኩረት ማድረግ ወሳኝ ነው" ብለዋል። አሁን ባለው ሁኔታም 75 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ35 ዓመት እድሜ በታች ያለና መስራት የሚችል እንዲሁም በአግባቡ ልንጠቀምበት የሚገባው ነው ሲሉም ተናግረዋል። የኃይል ዘርፉ ለማንኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደ ሞተር የሚያገለግል ቁልፍ መሆኑንና ለዚህም መንግስት ትልቁን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ለዚህም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመስራትና የውጭና የአገር ወስጥ የግሉ ዘርፍ ተሳታፊዎች በኃይል ዘርፍ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ማበረታታት አለብን ሲሉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የፕሮግራሙ ምክትል ኃላፊ ማቲያስ ሻውር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በኃይል አቅርቦትና ማምረት ዘርፍ ከፍተኛ ስራ የሰራች ቢሆንም 60 በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ ግን እስካሁን ተደራሽ አይደሉም ሲሉም ተናግረዋል። ለዚህም የግሉን ዘርፍ በማበረታታት ከአየር ንብረት ጋር የሚስማማ የኃይል አቅርቦትን ማስፋፋት ለሃገሪቷ ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ዛሬ የተከፈተው ሶስተኛው የኃይል ልማት ፕሮጀክትም ይህንኑ አማራጭ የኃይል አቅርቦት ለህዝቡ የማቅረብ፣ የግሉን ዘርፍ በተለያየ መንገድ የመደገፍና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችም ላይ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም