ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በውሀና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በውሀና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ
ህዳር 19/2012 ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በውሀና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ትናንት ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ከዩጋንዳ የውሃና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኪቱቱኪሞኖ ማርጋሬት ጋር ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ቀጠናዊ ጉዳዮች፣ ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችና የናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ተነስተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ አቶ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ያላቸውን የጋራ ሀብት በትብብርና በውጤታማነት ለመጠቀም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር አንዳለባቸው መግለጻቸውን አስታውቋል። ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባልነታቸው በቀጠናው ብልጽግና ለማምጣት የተሻለ እድል እንደሚሰጣቸው አቶ ታገሰ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ዩጋንዳ የናይል ወንዝን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የትብብር ማዕቀፉን ቀድመው መፈረማቸውና ማጽደቃቸውም ሌሎች አገሮች የእነሱን ፈለግ በመከተል የናይል ተፋሰስ የትብብር ኮሚሽንን ለመመስረት እንደሚያስችል ገልጸዋል። የኢትየጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁሉንም አገሮች ፍላጎት ባጣጣመ መልኩ እየተገነባ መሆኑንም አብራርተዋል። የዩጋንዳ የውሃና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኪቱቱኪሞኖ ማርጋሬት በበኩላቸው ኢትዮጵያና ዩጋንዳ የናይል ተፋሰስ አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅትም የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እውን እንዲሆን በተሻለ ትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። የመጀመሪያው የናይል ተፋሰስ የመሪዎች ጉባኤ በ2009 ዓ.ም በኢንቴቤ በተካሄደበት ወቅት ወንዙን በትብብር ለመጠቀም የሚያስችሉ ስትራቴጅያዊ ውሳኔዎችን በመሪዎች መተላለፉን በማስታወስ ውሳኔዎችን ለመፈጸምም ዩጋንዳ የበኩሏን እየተወጣች መሆኗን ገልጸዋል። ሁለቱ አገሮች ትብብራቸውን በውሀና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ይበልጥ ለማጠናከር ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑንም ተናግረዋል። ሁለቱ አገሮች የተፋሰስ ልማት፣ የአቅም ግንባታ፣ የመስኖ ልማት፣ የሀይል ማምረት፣ የአካባቢ ደህንነት ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚችሉም አስረድተዋል። የአፍሪካ አህጉር ህዝብ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የውሃ እጥረት እንዳይከሰት ሁሉንም የውሃ ሀብቶች በጋራና በትብብር በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን አማራጭ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያና ዩጋንዳ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሚያስችል ቀጠናዊ ትብብር እንዲመሰረት የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችል የተሻለ እድል እንዳላቸውም አንስተዋል።