ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን 30 በመቶ ማሳደጉን ገለጸ

ኢዜአ፤ህዳር 18/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ ስራውን 30 በመቶ በማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡን እያጠናከረ መሆኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የስካይ ትራክስ የባለ 4 ኮከብ ደረጃ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን መክፈቱን፣ እለታዊ የበረራ ቁጥሮችን መጨመሩንም ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ የአየር ማረፊያዎችን መሰረተ ልማት በማስፋፋትና በማዘመን፣ አዳዲስና ዘመናዊ በሆኑ አውሮፕላኖቹ የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች በማገናኘት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እያጠናከረ መሆኑን ጠቁሟል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈው የደንበኞች አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ለ2 ነጥብ 8 ሚሊየን የሀገር ውስጥ መንገደኞች የበረራ አገልግሎትን ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።

አየር መንገዱ የመንገደኞችና የጭነት አገልግሎትን በመስጠት የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን በተጨማሪም በተመጣጣኝ ክፍያ የሚሰጠውን የበረራ አገልግሎት ወደሌሎች የሀገሪቱ መዳረሻዎች ለማስፋፋት ዝግጅቱን አጠናቅቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም “አየር መንገዳችን የሀገር ውስጥ የበረራ አማራጮችን በማስፋትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የጉዞ አገልግሎት በመስጠት በሀገራችን የቱሪዝም እድገትም ሆነ በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ይጫወታል።” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 22 የሀገር ውስጥና 125 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ በቀን ከ51 በላይ፣ በሳምንት ደግሞ ከ350 በላይ የሀገር ውስጥ በረራዎችን በማቅረብ ደንበኞቹን በማገልገል ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም