ቀጥታ፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የህልውና ጉዳይ ነው ... ፕሬዝዳንት ሙሰቬኒ

ኢዜአ፤ ህዳር 18/2012  የዩጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሰቬኒ በዩጋንዳ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የልኡካን ቡድን አባላትን ዛሬ በካምፓላ በሚገኘው ጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሙሰቬኒ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የአፍርካን አህጉር ለማበልጸግ በኢኮኖሚ ማስተሳሳር የህልውና ጉዳይ ነው።

አፍሪካ እርስ በርስ ለመገበያየት የሚያስችል በርካታ ምርቶች ያሉት አህጉር መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ሙሰቬኒ፤ በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር የእርስ በእርስ ግብይቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያም እንደሚያደንቁ የገለጹት ፕሬዝዳንት ሙሰቬኒ፤ ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ግንኙነታቸውን በህዝብ ለህዝብና በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የጀመሩትን ስራ አጠናከረው መቀጠል አለባቸው ተብሏል።

የኢትዮጵያን የፐብሊክ ዲፕማሎሲ የልኡካን ቡድን የመሩት የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ አፍሪካን እንደ አህጉር ለማበልጸግ እያንዳንዱ አባል አገር ከራሱ አልፎ ለሌላው ማሰብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

አፍሪካ ከራሱ አህጉር ህዝብ በላይ የሚበቃ ሀብት እንዳለው ያነሱት አፈ ጉባኤ ታገሰ፤  ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ያለውን ክፍተት መሙላት ከተቻለ አፍሪካን ወደ ብልጽግና ማማ መውስድ ይቻላል ብለዋል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ዩጋንዳ የናይል የትብብር ማዕቀፍን በማጽደቅ በአፍሪካ ህብረት በሰነድነት ማስቀመጧ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን ለመመስረት ጥሩ እርምጃ በመሆኑ  ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም