እየተስፋፋ የመጣውን በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ለመከላከል የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
እየተስፋፋ የመጣውን በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ለመከላከል የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ተባለ
ህዳር 18/2012 የህይወት መጥፋትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመከላከል የመላው ዜጋ የጋራ ጥረት የግድ መሆኑን የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ። በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን ከትናንት ህዳር 15 ቀን 2012 ጀምሮ መከበር ጀምሯል። የዘንድሮው የነጭ ሪባን ቀን የሚከበረው "ሴቶችንና ህፃናትን ከጥቃት በመጠበቅ ሁላችንም ሃላፊነታችን እንወጣ በሚል መሪ ሐሳብ " እየተካሄደ ነው። የነጭ ሪባን ቀን ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት የሚከበር ዓለም አቀፍ በዓል ሲሆን ዓላማውም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ወንዶች አጋርነታቸውን የሚያረጋግጡበት ነው። እናም በሁለቱ ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወንዶች ነጭ ሪባን በደረታቸው ላይ በማድረግ ''ጥቃት አላደርስም፤ ሲያደርሱም አይቼ ዝም አልልም፤ ተባባሪም አልሆንም'' በማለት በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ ቃል ይገባሉ። በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት መሰረት 26 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። እነዚህ ጥቃቶች ከህይወት ማጣት ጀምሮ አደገኛ ለሆኑ በሽታዎችና የአካል መጉደል የሚዳረጉ መሆናቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዘንድሮው የነጭ ሪባን ቀን እየጨመረ የመጣውን የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል፤ በበሽታው የተያዙ ሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ይቸረው ዘንድ መልእክት እንደሚተላለፍ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ቀኑን ምክንያት በማድረግ በሰጠው መግለጫው አስታውቋል። ሚኒስትሯ ወይዘሮ የአለምጸሃይ አስፋዉ በዚሁ መግለጫቸው ሴቶች ህይወታቸውን እንዲያጡ፣ የአካል መጉደልና የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በሽታ ተጠቂ እንዲሆኑ የማድረግ ወንጀል እየተፈፀመማቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህንን ችግር ለመከላከል መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል። ህብረሰቡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ ተገቢውን ግንዛቤ አግኝቶ ከተግባሩ እንዲታቀብ ብሎም በተግባሩ የተሰማሩ አካላትን መከላከል እንዲችል እንዲሁም በሴቶች ላይ ጥቃት የፈፀሙ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በዚህ ረገድ ወንዶች በሴቶች ላይ ጥቃት ባለመፈፀምና የሚደርሰውንም ጥቃት በአጋርነት እንዲከላከሉ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ ቢሮ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠሪ ሚስ ሌቲ ትዋራ በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የመከላከል ስራ በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። በአጠቃላይ በዓለማችን ካሉት ሴቶች 50 በመቶ የሚሆኑት ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ከሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።