ቀጥታ፡

ኮስት የተባለው ዓለም አቀፍ ኢኒሸቲቭ የግንባታ ፕሮጀክቶችን አሠራር ግልጸኝነት የሚደግፍ መረጃ ማውጣት ጀመረ

ህዳር 18/2012 ኮንስትራክሽን ሴክተር ትራንስፓረንሲ ኢኒሸቲቭ (ኮስት) የተባለው ተቋም በኢትዮጵያ የግንባታ ፕሮጀክቶችን የአሰራር ግልጸኝነት የሚደግፍ መረጃ ይፋ ማድረግ ጀመረ። በአገሪቷ ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶችም የዲዛይን ጥናት ችግሮችና በታቀደለት የጊዜ ገደብ አለማጠናቀቅ እንደሚስተዋልባቸው ገለጿል። ኢኒሸቲቩ ዛሬ  በሰባት ፕሮጀክቶች ላይ ያካሄዳቸውን የጥናቱን መረጃ ይፋ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል። በምህጻረ ቃሉ ኮስት( construction sector transparncy intiative) ኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀው ተቋም የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እያሱ ይመር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ከዓለም ባንክና 'ዲፌድ' በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ የግንባታ ዘርፎች ላይ የአዋጭነትና የመረጃ ማውጣት ጥናት የሚሰራ ተቋም ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 አባል አገራትን የያዘ ዓለም አቀፍ ተቋምም ነው። ዋና ዓላማውም በግንባታው ዘርፍ እየተፈጸሙ ያሉ ስራዎችን በተለይም የመንግስት ፕሮጀክቶችን መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። መረጃዎችንም በመተንተን ለሚመለከታቸው አካላት በማቅርብ ዘርፉ እንዲሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየሰራ ይገኛል ተብሏል። ዛሬም በሰባት ፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነትና የግልጸኝነት ጥናት አድርጎ ስምንት መረጃዎችን አቅርቧል። በዚህም መሰረት ፕሮጀክቶቹ የዲዛይን ጥናት ጉድለትና በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ ችግር እንደሚታይባቸው በኢኒሸቲቩ የፕሮጀክቶች አጥኚ ባለሙያ ያረጋል አሊ ተናግረዋል። ጥናቱ ፕሮጀክቶቹ ከአዋጭነት ጥናታቸው ጀምሮ የጨረታ ሂደቱ፣ የትግበራ፣ የአፈጻጸም ሂደቶች ምን ይመስላሉ? የሚሉትን በማካተት እንደሚሰራና በግኝቶቹ መሰረትም ፕሮጀክቶቹን በቀጣይ የበለጠ ማዳበርና የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ማስቻል እንደሆነም ተናግረዋል። በውይይቱ ከተገኙት ባለድርሻ አካላትና ከአስተባበሪዎቹ መካከል እንዱ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነው። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መንግስት የአገሪቷን የመሰረተ ልማት አውታሮች ለማስፋፋት በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች ከፍተኛ ወጪ መድቦ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው። በትራንስፖርት ዘርፍ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የነፋስና የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ዘርፍ፣ በግንባታ ዘርፍ እንዲሁም በኢንዱስትሪ መንደርና በፋብሪካ ፕሮጀክቶችን እየገነባ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል። በመሆኑም ኢኒሸቲቩ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማት አውታሮች ለታለመላቸው አላማ ስለመዋላቸው በቅርብ በመከታተልና መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የግልጽኝነትና የተጠያቂነትን አሰራር ከማስፈን አንጻር የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም ኢትዮጵያ በመንግስት የወጪ አሰራርን ግልጽ ከማድረግ አንጻር ካላት ቁርጠኛ አቋም ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራች እንደሆነም ጠቅሰዋል። በዚህም የመንገድ፣ የውሃና ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶችን መረጃ ይፋ በማድርግ ክፍተቶችን የማጣራትና የቴክኒክ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጪዎችን ለማዳን ስራዎችን እያከናወነ ነውም ብለዋል። የኢኒሸቲቩ መረጃም ከመንግስት፣ ከግልና ከሌሎች ማህበራት የተመጣጠነ ውክልና ባላቸው አካላት የሚያወጧቸው በመሆናቸውም ተኣማኒነት እንዳላቸውም ገልጸዋል። ይህንን መረጃ የመግለጽና ምላሽ የማስተናገድ እንዲያግዙ ፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የአፈጻጸም ጥራት ለመለየትና ክፍተቶችን ለማስተካከል እንደሚረዳም ያምናሉ። አሠራሩም የሁሉም ተቋማት ባህሪ እንዲሆን ለማድረግም በዘርፉ የህግ ማዕቀፍ እንዲደገፍ በመንግስት ግዥ መመሪያ እንዲካተት ሆኗል ብለዋል። በህዝብ ሀብት የሚከናወን ማንኛውም ግዥ አፈጻጸሙ የግልጸኝነትና ተጠያቂነት መርህ የተከተለ እንዲሆንም  መንግስት ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም ተናግረዋል። በመሆኑም ይህንን መርህ ተግበራዊ ለማድረግም በሚከናወኑ ተግባራት የመንግስት ድጋፍ እንደማይለየው ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ኢኒሸቲቩ ዓለም አቀፍ አሰራርና መርህ ያለው ሲሆን ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በስምንት አገራት የተጀመረና በግንባታዎች ዘርፍ የአሠራር ግልጸኝነት መርህ የሚደግፍ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም