ከስርዓተ-ጾታ፣ ከእናቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት ማህበረሰቡን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከስርዓተ-ጾታ፣ ከእናቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት ማህበረሰቡን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል
ህዳር 18/2012 በኢትዮጵያ ከስርዓት-ጾታ፣ ከእናቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት በችግሮቹ ዙሪያ ማህበረሰቡን በማስተማር የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተገለፀ። በኢትዮጵያ ከስርዓተ ፆታ ጋር በተያያዘና በሌሎች ባህላዊ የተዛቡ አመለካከቶች ሳቢያ እናቶችና ህፃናት ለተለያዩ ማህበራዊና ስነ-ልባናዊ ችግሮች እንደሚዳረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህም የእናቶችንና ህጻናት ጤና ጉዳይን አሳሳቢ እንዲሆን እያደረገው እንደሆነም እንዲሁ። በአገራዊ እድገት ላይ ጭምር ጫና የሚያሳድረውን ይህንን ችግር ለመከላከል በተለያዩ አካላት የሚደረገው ጥረት የተዛቡ አመለካከቶችን በማረቅ ላይ ጭምር ማተኮር እንዳለበትም ብዙዎች ያሳስባሉ። በዚህ ረገድ ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው ተብለው የሚታሰቡት የሃይማኖት ተቋማት ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ የስነ-መለኮት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፍቃዱ ማቲዎስ ገልፀዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የገለፁት ትምህርት ቤቱ በሥርዓተ-ጾታ ልማት፤ ሥነ-ተዋልዶ ጤናና ሥነ መለኮት ርዕስ ጉዳዮች ላይ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው። በውይይቱ ላይ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል። ዶክተር ፍቃደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት የመጽሐፍ ቅዱስና መንፈሳዊ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር ከስርዓት-ጾታ እኩልነት፣ ከእናቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመከላከል በችግሮቹ ዙሪያ ማህበረሰቡን በማስተማር የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእናቶችና ህጻናት የጤናና የኑሮ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የሁሉም አካላት ትብብርና ርብርብ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ የስነ-መለኮት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ከስርዓት-ጾታ እኩልነት፣ ከእናቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ የሚያከናውናቸውን የልማት ሥራዎች በተመለከተ ገለፃ ተደርጓል። በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ አማኑኤል አበራ የእምነት ተቋማት ዘላቂ ልማትን ከማሳካትና የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት አገልግሎት ከመስጠት አንጻር በርካታ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ የሚከናወኑት ተግባራት በቂ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ካላቸው የኢኮኖሚ አቅምና የሰው ሃይል እጥረት የመነጨ ነው ብለዋል። በመሆኑም እምነትን መሰረት ያደረጉ የልማት ተቋማት ያላቸውን የሰው ሃይልና የገንዘብ አቅም በማቀናጀት በተለይ የሴቶችንና ህናጻትን ጤና ለማሻሻል ብሎም ደህንነታቸውን ለመጠበቅ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነውን ተግባር ማገዝ ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።