እየተጋጋለ ለመጣው የብሄርተኝነት ስሜት ፍትሐዊ የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት መፍትሄ ነው - ኢዜአ አማርኛ
እየተጋጋለ ለመጣው የብሄርተኝነት ስሜት ፍትሐዊ የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት መፍትሄ ነው
ህዳር 18/2012 እየተጋጋለ ለመጣው የብሄርተኝነት ስሜት ፍትሐዊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት መፍትሄ መሆኑ ተገለጸ። የዋለልኝ መኮንን "የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ" በሚል ርእስ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል። ዋለልኝ መኰንን የኢትዮጵያን አርሶ አደሮችና ላብ አደሮች ነፃ ለማውጣት በ1960ዎቹ ውስጥ በተደረገው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትግል ዓብይ ሚና ከተጫወቱ መካከል ግንባር ቀደሙ መሆኑ ይታወቃል። ዋለልኝ "የብሔረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ" የሚልና እስካሁን አነጋጋሪ ሆኖ የቀጠለን ጽሁፍ የፃፈ ሲሆን፤ የማርክሲስት አመለካከት የነበረውና በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ ያመነው “የብሄረሰቦች ጭቆና” በተባበረ የህዝብ አመፅና በሶሻሊስት ፖለቲካዊ ርዮተ-ዓለም ብቻ ሊፈታ ይችላል የሚል እምነትም ነበረው። ብሄራዊ ጭቆናውን ለማስረዳትም "ኢትዮጵያዊ ማን ነው? የዜግነት ጉዳይና ኢትዮጵያ ከምን ከምን ነው የተሰራችው? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ከ50 ዓመት በፊት በፃፈው ጽሁፍ አመላክቷል። ይህን ተከትሎም ከ50 ዓመታት በፊት በዋለልኝ መኮንን የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የተመለከተው ባለ 5 ገጽ ጽሑፍ ውስጥ ያሉ እሳቤዎች ያሳደሩትን ተፅዕኖ የሚፈትሸ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። በውይይት መድረኩ ላይ ፕሮፌሰር ማርታ ኳዊ ኩምሳ፣ እጩ ዶክተር ስሜነህ አያሌው፣ ዶክተር ዲማ ነጎ፣ አቶ ታምራት ከበደ እንዲሁም ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ ንግግር አቅርበዋል። ምሁራኑ በንግግራቸው የዋለልኝ 50 ዓመታትን የተሻገሩ እሳቤዎች አሁንም ገዝፈው እንደሚታዩ በመግለጽ፤ ላለፉት ሶስት አስርተ ዓመታት እየተተገበረ ባለው ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ዘይቤም አነጋጋሪና አከራካሪ እንደሆነ ቀጥሏል ብለዋል። አገረ መንግስት፣ ውቅረ መንግስት፣ ብሄርተኝነት የመሳሰሉና እየተጋጋሉ ያሉ ጉዳዮች አሁንም ድረስ ያልተፈቱና አጨቃጫቂ ጉዳዮች በመሆናቸውም ለምን በ50 ዓመት ውስጥ ሊመለሱ አልቻሉም? የሚሉ ሀሰቦችን አንስተው መወያየት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚረዳም ያላቸውን አምነት አስረድተዋል። ዶክተር ሰሚር ዩሱፍ፤ የብሔርተኝነት ስሜት እስካሁን ድረስ ጥያቄ የሆነው ህዝቦች ስለተዋደቁለትና ስለሞቱለት መሆኑንና ህዝባዊ መሰረት ያለው በመሆኑም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህ አሁን ድረስ እየተጋጋለ ለመጣው የብሄርተኝነት ስሜትም መፍትሄ ለመስጠት ፍትሐዊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል ዶክተር ሰሚር። በውይይት መድረኩ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ነበሩ።