ቀጥታ፡

የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የፈጠራ ስራና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መስራት ይፈልጋሉ

ህዳር 18/2012 የጀርመኗ የባንድን ቩርትምበርግ ግዛት ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በፈጠራ ስራና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ። አዲስ አበባ የተገኙት የባንድን ቩርትምበርግ ግዛት የልዑካን ቡድን ዛሬ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ገላጸ ተደርጎላቸዋል። የግዛቷ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ኒኮላ ሆፉሚስትር እንደገለጹት በርካታ የአገራቸው ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት አመራጮች ባሏት ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት አላቸው። በተለይ የግዛቲቷ ባለሃብቶች በፈጠራ ስራና በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አብራርተዋል። ኢትዮጵያ የባለሃብቶችን ቀልብ በመሳብ ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚ መሆኗንም አውስተዋል። ሚንስትሯ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ኃይል ለማድረግ እየሰሩ ያለውን ስራም አድንቀዋል። 35 የግዛቲቱ ባለሃብቶች፣ የተቋማት ተወካዮች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች አካላት በአዲስ አበባ ቆይታቸው  የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ይጎበኛሉ ተብሏል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ አገሪቷ በርካታ የቴክኖሎጂ ዘርፍ  የኢንቨስትመንት አማራጭና የሰው ኃይል እንዳላትና 70 በመቶ የሚጠጋው ሕዝቧ ከ30 ዓመት በታች የሆነ አምራች ዜጋ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ 29 ሚሊዮን ተማሪዎች እንደሚገኙ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ባለሃብቶች በሚሰማሩባቸው መስኮች የተሻለ የሰው ኃይል ያገኛሉ ብለዋል። የውጭ አገር ባለሃብቶችን ለመሳብ ምቹ ፖሊሲ እና ተስማሚ ሕጎች መቀረጻቸውንም ተናግረዋል። በተገነቡ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አብራርተዋል። እንደ ዶክተር ጌታሁን ገለጻ ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያስፈልጋታል። ጀርመን በዓለም ላይ ከሚገኙ የተሻለ የቴክኖሎጂ አቅም ካላቸው አገራት ተርታ በመሆኗ የባለሃብቶቿ መምጣት ኢትዮጵያ ለያዘችው የቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽን አቅም ግንባታ ከፍተኛ እገዛ አለው። በቴክኖሎጂ ከፍተኛ እውቅናን ያተረፈችው የባንድን ቩርትምበርግ ግዛት 203 ቢሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ገቢ እንዳላት ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም